የኬኒያ፣ የሞሪታኒያ እና የኬፕቬርዴ ፕሬዚደንቶች ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ ገብተዋል - ኢዜአ አማርኛ
የኬኒያ፣ የሞሪታኒያ እና የኬፕቬርዴ ፕሬዚደንቶች ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ ገብተዋል
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 10/2015 በ36ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ለመሳተፍ የኬኒያ፣ የሞሪታኒያ እና የኬፕ ቬርዴ ፕሬዚደንቶች አዲስ አበባ ዛሬ ማለዳ ገብተዋል።
ፕሬዚደንቶቹ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
በዚህም የኬኒያ ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶን የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሀመድ፥ የሞሪታኒያ ፕሬዝዳንት ሙሀመድ ኦልድ ጋውዛኒን የገቢዎች ሚኒስትሯ አይናለም ንጉሴ፣ የኬፕቬርዴ ፕሬዚደንት ጆሴ ማሪያ ፔሬ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬና ሌሎች የመንግስት የስራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የአፍሪካ ሕብረት አባል አገራት "የህብረቱ ስራ አስፈጻሚዎች ስብሰባ" ባለፉት ሁለት ቀናት የተካሄደ ሲሆን ሀገራቱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው አማካኝነት የጎንዮሽ እና የሁለትዮሽ ጉዳዮችን የሚያጠናክሩ ቀጣናዊ እና አህጉራዊ ምክክሮችም በመካሄድ ላይ ይገኛሉ።
36ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤም በመጪው ቅዳሜና እሁድ "የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራን ማፋጠን" በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄድ ይሆናል።
በጉባኤ የሚሳተፉ መሪዎች ከትናንት ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ እየገቡ ሲሆን እስከ አሁንም ማለዳ የገቡትን ጨምሮ የሴራሊዮን፣ የኮሞሮስ፣ የቡሩንዲ፣ የታንዛኒያ፣ የሩዋንዳ፣ የሌሴቶ፣ የናይጀሪያ ፕሬዚዳንቶች አዲስ አበባ ገብተዋል።
እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ የሊቢያ፣ የኡጋንዳ እና የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዚዳንቶች እና የሌሎች የአፍሪካ አገራት መሪዎች መዲናዋ አዲስ አበባ ገብተዋል።