የኢትዮጵያ ሕዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም የመልካም አስተዳደር ችግሮች እልባት እንዲያገኙ እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሕዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም የመልካም አስተዳደር ችግሮች እልባት እንዲያገኙ እየሰራ ነው
ደብረ ብርሃን (ኢዜአ ) የካቲት 9/2015 የኢትዮጵያ ሕዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም በየደረጃው የተፈጠሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እልባት እንዲያገኙ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም የ2015 ዓ.ም ግማሽ የበጀት ዓመት የእቅድ ክንውን አፈፃፀም ግምገማ በደብረ ብርሃን ከተማ እያካሄደ ነው።
ተቋሙ በየደረጃው የተፈጠሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እልባት እንዲያገኙ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የተቋሙ ዋና እምባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ ገልጸዋል።
ተቋሙ ከ40 ሺህ ከሚበልጡ ዜጎች አቤቱታዎችን መቀበሉን ጠቅሰው፤ በግማሽ ዓመቱ ከቀረቡት አቤቱታዎች ውስጥ 1 ሺህ በላይ የሚሆኑትን የማየት ስልጣን ያለው በመሆናቸው ህጋዊ እልባት እንዲያገኙ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ዶክተር እንዳለ አክለውም ቀሪዎቹ አቤቱታዎች ደረጃቸውን ጠብቀው ባለመቅረባቸው አቤቱታዎቹን ለአቀረቡ ወገኖች የህግ ምክር አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል።
በተቋሙ ባለፉት ስድስት ወራት ተቀባይነት ያገኙትንና ከ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት የዞሩ አቤቱታዎችን በማደራጀት በ1 ሺህ 174 መዝገቦች ላይ ተገቢውን ምርመራ አድርጎ በማጣራትና ክስ በመመስረት 741 መዝገቦች እልባት ማግኘታቸውን አስረድተዋል።
በቀሪዎቹ መዝገቦች ላይ ምርመራ እየተካሄደ ሲሆን፤ የቀረቡት አቤቱታዎች ከስራ ምድባ፣ ዝውውርና የደረጃ እድገት፣ ከመንግስት ተቋማት ተገቢውን አገልግሎት አለማግኘት፣ ከመሬት ይዞታና ካሳ ክፍያ ጋር የሚያያዙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ዶክተር እንዳለ አያይዘውም ተበዳዮች 1 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ምትክ እንዲያገኙ፣ ያልተከፈለ 726ሺህ ብር የወር ደሞዝ እንዲከፈል እና የሶስት ተማሪዎች በከፍተኛ የትምህርት ተቋም ምደባ እንዲስተካከል መደረጉ ተቋሙ ባለፉት ስድስት ወራት ካከናወናቸው ተግባራት መካከል ዋነኞቹ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በየደረጃው የሚፈፀሙ የአስተዳደር በደሎችንና ሌሎች የህዝብ ጥያቄዎች እንዲፈቱ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው ጠቁመው፤ ዜጎችም አድሏዊ አሰራሮች ሲገጥማቸው በአቅራቢያቸው በሚገኙት የሕዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም ቀርበው እንዲያመለክቱ አሳስበዋል።
በተቋሙ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት እምባ ጠባቂ አቶ ጋሻነው ደሴ በበኩላቸው ባለፉት ስድስት ወራት ከ20 ሺህ ከሚበልጡ ዜጎች አቤቱታዎችን መቅረባቸው ጠቅሰዋል።
እምባ ጠባቂው አክለውም ተደራጅተው ከቀረቡት በ812 መዝገቦች ውስጥ 319ኙ መዝገቦች እልባት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለመገንባት እየተደረገ ላለው ጥረት ስኬት ሁሉም አካላት ሊተባበር እንደሚገባም አቶ ጋሻነው አመልክተዋል።
የአሶሳ ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት እምባ ጠባቂ አቶ ፈቃዱ ታደሰ እንዳሉት ዜጎች መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው የሚያቀርቧቸውን አቤቱታዎች እልባት እንዲያገኙ በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው።
በዚሁ ነገ በሚጠናቀቀው የእቅድ ክንውን አፈፃፀም ግምገማ ከዋናው ተቋምና ከቅርንጫፍ ተቋማት የተውጣጡ አመራሮችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው።