ቀጥታ፡

በላል ይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ላይ ያንዣበበውን አደጋ ለማስገንዘብ ሰላማዊ ሰልፍ ሊደረግ ነው

ወልዲያ መስከረም 25/1/2011 በላል ይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የተገነባው መጠለያ በቅርሱ ላይ አደጋ እንዲያንዣብብ ማድረጉን ለማስገንዘብና ትኩረት እንዲሰጠው ለማድርግ በመጪው እሁድ በላል ይበላ ከተማ ሰለማዊ ሰልፍ እንደሚካሄድ ተገለጸ። የላል ይበላ አድባራት አስተዳዳሪ መምህር አባ ጽጌ ሥላሴ እንደገለጹት ከ10 ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በአራቱ ላይ ቀደም ብሎ መጠለያ መገንባቱን አስታውሰዋል። በአውሮፓ ሕብረት የገንዘብ ድጋፍ ለአምስት ዓመት ያገለግላል ተብሎ በጊዜያዊነት የተሰሩ መጠለያዎች በአሁኑ ወቅት ከ10 ዓመት በላይ እንደሆናቸው ተናግረዋል፡፡ ግዙፍ ብረቶችን የተሸከሙት ምሰሶዎች ቦታቸውን እየለቀቁ በመሆኑ በቅርሱ አናት ላይ የተላለፉት ከባድ ብረቶች በንፋስ ኃይል ተገፍተው ቢወድቁ ቅርሱን ይጎዱታል በሚል የአካባቢው ህዝብ ከፍተኛ ስጋት ላይ መውደቁን ተናግሯል። ባለፉት ዓመታት ከክልል እስከ ፌደራል መንግስት ከዚያም አልፎ በዩኒስኮ ደረጃ ችግሩ አሳሳቢ መሆኑ ቢታመንበትም ጥናት ከማካሄድ ውጭ ተግባራዊ ምላሽ ሳይሰጥ መቆየቱ ስጋት መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡ መጠለያዎቹን የሰራው "ኢንዴኮ" የተባለ የጣሊያን ድርጅት በቅርሶቹ ላይ የተሰራውን መጠለያ ለማንሳት 300 ሚሊዮን ብር በጀት እንደሚጠይቅ ቢገልጽም እስካሁን ጉዳዩ መፍትሄ አለማግኘቱን ጠቁመዋል። ፈጣን መፍትሄ ባልተሰጠ ቁጥር ምትክ የለሹ የላል ይበላ ቅርስ ለአደጋ ይዳረጋል የሚለው ሥጋት በማየሉ በሕዝቡ ግፊት የችግሩን አሳሳቢነት ለሚመለከታቸው አካላት ለማሳወቅ ሰልፉ መዘጋጀቱን ተናግረዋል። " የል ይበላ ቅርስ የአገር ሃብት በመሆኑ መንግስትና ባለድርሻ አካላት በጥናቱ የተጠየቀውን በጀት በመመደብ በቅርሱ ላይ አደጋ ከመድረሱ በፊት ተግባራዊ ምላሽ እንዲሰጡ ለማሳሰብ ጭምር የሚደረግ ሰልፍ መሆኑንም” አባ ጽጌ አክለው ገልጸዋል፡፡ የላል ይበላ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊና የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ  አቶ ኃይሌ ንጋቴ በበኩላቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች ባጠኑት መሰረት መጠለያው ሲሰራ የነበረው የነፋስ ፍጥነት በአሁኑ ወቅት ከእጥፍ በላይ ጨምሯል። "ቅርሱ አደጋ የተጋረጠበት ስለመሆኑ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርም ሆነ ዩኔስኮ ያምናሉ ነገር ግን ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ መስጠት ባለመቻሉ ህዝቡ ኮሚቴ አዋቅሮ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ተዘጋጅቷለ " ሲሉ ተናግረዋል። በከተማው አስተዳደር በኩል ሰላማዊ ሰልፉ እንዲካሄው ፍቃድ መሰጠቱንም ተናግረዋል። ከባድ ብረት የተሸከመው መጠለያ ተነስቶ ቀላል በሆነና ቅርሱን ሊጎዳ በማይችል መጠለያ መተካት አሊያም የቅርሶቹን ጣራ መጠገን አማራጭ መፍትሄ መሆኑንም አቶ ኃይሌ ጠቁመዋል፡፡ በመጭው እሁድ የሚካሄደውን ሰልፍ የሚያስተባብረው ኮሚቴ ሰብሳቢ ወጣት መስፍን ጌታመሳይ በበኩሉ በሰጠው አስተያየት ቅርሱ ላይ የተጋረጠው አደጋ ጊዜ የማይሰጥ መሆኑን ተናግሯል። መንግስትና ባላድርሻ አካላት ጉዳዩን አውቀው ተግባራዊ እርምጃ እንዲወስዱ ሰላማዊ ሰልፉ መዘጋጀቱን አስረድተዋል፡፡ የላል ይበላ ከተማም ሆነ የአካባቢው ሕዝብ በሰልፉ ላይ በስፋት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስተባበሪው ገለጿል። በክልሉም ሆነ በአገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ የብዙሀን መገናኛዎች ሰላማዊ ሰልፉን በመዘገብ የችግሩን አሳሳቢነት ለዓለም ህዝብ እንዲያስተዋውቁ ጥሪ መደረጉንም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም