በኢትዮጵያ የሚቲዎሮሎጂ መሰረተ ልማቶችን በማዘመን የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት አስጣጥን የተሳለጠ ለማድረግ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የሚቲዎሮሎጂ መሰረተ ልማቶችን በማዘመን የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት አስጣጥን የተሳለጠ ለማድረግ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 9/2015 በኢትዮጵያ የሚቲዎሮሎጂ መሰረተ ልማቶችን በማዘመን የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት አስጣጥን የተሳለጠ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለፀ።
በዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት 18ኛው የአፍሪካ ቀጠናዊ ትብብር ማኅበር 54 አባል አገራት የሚሳተፉበት ኮንፍረንስ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
የዓለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት ዋና ፀሐፊ ኘሮፌሰር ፒተር ታላስ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ አሁን ላይ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ተባብሶ ቀጥሏል።
በመሆኑም የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን ወቅታዊና ተዓማኒ የሚቲዎሮሎጂ ቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ በመስጠት ተጽዕኖውን መቋቋም ይገባል ነው ያሉት።
በዓለም ያለውን የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው ድርጅቱም በተለይም በአፍሪካ የዘርፉን እድገት ለማጠናከር ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚንስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ በበኩላቸው፤ ዓለም አደገኛና አስቸጋሪ የአየር ንብረት ለውጦችን እየተጋፈጠች ትገኛለች ብለዋል።
ይህም ችግር በተለይም በአፍሪካ ላይ የሚያደርሰው አሉታዊ ጫና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጦችን ለመቋቋም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ነድፋ እየሰራች መሆኑን ገልጸው በተለይም የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመከላከል ቅድመ ማስጠንቀቂያ አስፈላጊ መሆኑ ተናግረዋል።
ለዚህም ደግሞ የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት አሰጣጡን ማዘመን እንደሚገባ በመጠቆም።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና ተጽዕኖውን ለመቋቋም ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።
በአፍሪካ የሚሰጠውን የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት የተሻለ ለማድረግና ጥራት ያለው፣ ታማኝና ተደራሽ ለማድረግ በጋራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም በባለሙያዎች አቅም ግንባታ፣ በዘመናዊ የሚቲዎሮሎጂ መሳሪያዎች ተደራሽነት እንዲሁም ሁሉን አቀፍ የሚቲዎሮሎጂ መሰረተ ልማቶችን የማዘመን ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።