ቀጥታ፡

በሽታን የሚቋቋሙ የሰብል ዝርያዎችን በምርምር ለማውጣት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ገለጸ

አዳማ (ኢዜአ) የካቲት 09/2015 በሽታን መቋቋም የሚችሉ የሰብል ዝርያዎች በምርምር የማውጣት ስራ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ገለጸ።

ለሰብል ምርታማነት ዕድገት ማነቆ የሆኑ ሙጃ፣ ሲናርና ጌንጭ የተባሉ አረሞችን መቆጣጠር በሚቻልበት ሂደት ላይ ያተኮረ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው። 

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሰብልና እፀዋት ተመራማሪ ዶክተር ጀማል ቶላ በመድረኩ እንዳሉት፤ ከዋግ በሽታ ጋር ተመሳሳይነት ያለው የስንዴ ራስ አድርቅ በሽታ እየታየ ነው። 

በሽታው ሰብሉ አብቦ ፍሬ ወደ መስጠት ሲቃረብ የሚያጠቃና ምርታማነትን የሚቀንስ መሆኑን ተናግረዋል።  

በሽታው ምርትና ምርታማነት ላይ የሚያመጣውን ተፅዕኖ መቋቋም የሚያስችሉ ተሞክሮዎችን በመውሰድ ለመከላከልና መድሃኒቶች ወደ ሀገር በማስገባት አገልግሎት ላይ እንዲውሉ እየተደረገ ነው ብለዋል። 

በተጨማሪም በሽታውን በትክክል የመለየትና መከላከል የሚያስችሉ መድሀኒቶችን መምረጥ እና በሽታውን መቋቋም የሚችሉ የሰብል ዝሪያዎች በምርምር ለማውጣት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

በሽታ በስፋት በታየባቸው አርሲና ባሌ ዞኖች የመከላከያ ኤክስቴንሽን ላይ አርሶ አደሮች በዕውቀት የተደገፈ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ከ800 በላይ ለሆኑ ባለሙያዎች ስልጠና መስጠቱን አስረድተዋል። 

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ ዶክተር ደጀኔ ሂርጳ በበኩላቸው፤ የስንዴ በሽታን ጨምሮ ሙጃ፣ ሲናርና ጌንጭ የተባሉ አረሞችን ለመቆጣጠር በመንግስት አቅም ብቻ በቂ ባለመሆኑ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ መጠናከር እንደሚገባ አመልክተዋል። 

በተለይ የስንዴ በሽታን ለመቆጣጠር አርሶ አደሩ ገበያ ላይ ያለውን መድሃኒት ሳይሆን በኤክስቴንሽን ሰንሰለት ውስጥ ያለፉ በግብርና ሚኒስቴር ተመዝግበው ምስክርነት የተሰጣቸውንና ዕውቅና ያላቸውን መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል። 

የፀረ አረምና ፀረ-ተባይ አስመጪ ድርጅት ስራ አስኪይጅ አቶ ሄኖክ ታዬ፤ የስንዴ በሽታን ጨምሮ የዋግ፣ የሙጃ፣ ሲናርና ጌንጭ አረሞች መድሃኒት በሠርቶ ማሳያ በተሟላ የኤክስቴንሽን አገልግሎት ፓኬጅ አርሶ አደሩ እንዲጠቀም እያሰራጨን ነው ብለዋል። 

ዘንድሮ በምዕራብ አርሲ ዞን አዳባ ወረዳና በምስራቅ ባሌ ጊኒር ወረዳ ከመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት ውጤታማ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ በሽታውን ተቋቁሞ በሄክታር እስከ 72 ኩንታል ማግኘት መቻሉንም ጠቁመዋል። 

በምዕራብ አርሲ ዞን የአዳባ ወረዳ አርሶ አደር ጌቱ ቢቂላ በሰጡት አስተያየት፤ በተሟላ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት የተደገፈ ጸረ-አረምና ጸረ-ተባይ መድሀኒቶች በመጠቀማችን ውጤታማ ሆነናል ብለዋል። 

በዚህም በሽታን በመቆጣጠር በሄክታር ከ50 ኩንታል በላይ ማግኘታቸውን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም