ቀጥታ፡

ለአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ ቀልጣፋ የቴሌኮም አገልግሎት ተደራሽ የሚያደርጉ ስራዎች ተከናውነዋል- ኢትዮ ቴሌኮም

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 9/2015 ለአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ ቀልጣፋ የቴሌኮም አገልግሎት ተደራሽ የሚያደርጉ ስራዎች መከናወናቸውን ኢትዮ ቴሌኮም አስታወቀ፡፡

በአፍሪካ ሕብረት የመሪዎችና ስራ አስፈጻሚዎች ስብሰባ የሚሳተፉ እንግዶች በኤምባሲዎች፣ ሆቴሎችና ሌሎችም ስፍራዎች ምቹ የቴሌኮም አገልግሎት የሚያገኙባቸውን ተግባራት ከዓለም አቀፍ የዘርፉ ተቋማት ጋር ማከናወኑንም ነው ኢትዮ ቴሌኮም የገለጸው፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በቦሌ አለም አቀፍ አየር መንገድ ማረፊያና በሆቴሎች እንዲሁም በአፍሪካ ህብረት ቅጥር ግቢ ውስጥ በውጭ ምንዛሬ ክፍያ የተለያዩ የቴሌኮም አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል።

ኢትዮ ቴሌኮም በ36ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች እና በ42ኛው የስራ አስፈጻሚዎች ስብሰባ የእንግዶቹን ፍላጎት የሚመጥን ዝግጅት ማድረጉም ተገልጿል፡፡

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኩባንያው ከፍተኛ የኮሚኒኬሽን ባለሙያ መሳይ ውብሸት የአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ በኢንተርኔት ትስስርና በሌሎችም የቴሌኮም አገልግሎቶች ሰፊ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

በተለይም በአፍሪካ ሕብረት ቅጥር ጊቢ ውስጥ የቴሌኮም መሰረተ ልማቶችን አቅም በከፍተኛ ደረጃ የማሳደግ ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።

በስብሰባ ማዕከሉና እንግዶች በሚያርፉባቸው ስፍራዎች ምንም አይንት የኢንተርኔት መቆራረጥ እንዳይኖር የ24 ሰዓት የክትትልና የቁጥጥር ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል ብለዋል።

በሌላ በኩል የስብሰባው ተሳታፊዎች ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ በኢትዮጵያ ሲም ካርድ መጠቀም እንዲችሉ ለአንድ ወር የሚቆይ ሲም ካርድ በውጭ ምንዛሬ ክፍያ መቅረቡንም ተናግረዋል፡፡

ተሳታፊዎች ይዘዋቸው የሚመጡትንም ሲምካርዶች በኢትዮጵያ መስመር እንዲጠቀሙ የሚያስችሉ ስራዎች ከዓለም አቀፍ የዘርፉ አጋር አካላት ጋር መከናወኑንም አክለው ገልጸዋል።

በኤምባሲዎች፣ በሆቴሎችና እንግዶቹ የሚያርፉባቸውን ስፍራዎች በመለየት በነጻ የፊክስድ ኢንተርኔት አገልግሎት(ዋይፋይን) በእጥፍ የማሳደግ ስራ መከናወኑንም ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በተመረጡ ሆቴሎች በውጭ ምንዛሬ የሲም ካርድ ሽያጭና ሌሎች አገልግሎቶች እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የቀረቡት የኢንተርኔትና ሌሎች አገልግሎቶች እስከ 90 በመቶ የሚደርስ ቅናሽ የተደረገባቸው መሆኑንም ኢትዮ ቴሌኮም ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም