ኢትዮጵያ ከናሚቢያ ጋር በወታደራዊ አቅም ግንባታ ዘርፍ ያላትን ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች- የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከናሚቢያ ጋር በወታደራዊ አቅም ግንባታ ዘርፍ ያላትን ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች- የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 9/2015 ኢትዮጵያ ከናሚቢያ ጋር በወታደራዊ አቅም ግንባታ ዘርፍ ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ ገለጹ፡፡
ኢትዮጵያና ናሚቢያ በወታደራዊ አቅም ግንባታ፣ በአየር ኃይል እና ባህር ሃይል ስልጠና በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡
የኢፌደሪ መከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ እና የናሚቢያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የዓለም አቀፍ ግንኙነትና ትብብር ሚኒስትር ኔቱምቦ ናንዲ ንዳይትዋህ ስምምነቱን ተፈራርመዋል።
ሁለቱ ሀገራት የቆየ የዲፕሎማሲ ትስስር እንዳላቸውም ዶክተር አብርሃም አስታውሰዋል፡፡
ከዚህ አኳያ ስምምነቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የቆየ ግንኙነት ከማጎልበት ባሻገር በመከላከያና ጸጥታ ጉዳዮች ያላቸውን ትብብር ይበልጥ የሚያጠናክር ነው ብለዋል፡፡
በመግበቢያ ሰነዱ ስምምነት መሰረት ሁለቱ ሀገራት በወታደራዊ አቅም ግንባታ ስልጠና፣ በአየር ኃይል፣ ባህር ሃይልና ሌሎች ዘርፎች በጋራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪ ስምምነቱ ሽብርተኝነትን ለመከላከል ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡
የናሚቢያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የዓለም አቀፍ ግንኙነትና ትብብር ሚኒስትር ኔቱምቦ ናንዲ ንዳይትዋህ፤ ሁለቱ አገራት ረዥም ዘመናትን ያስቆጠረ ወዳጅነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ በወታደራዊ ስልጠና፣ የመረጃ ልውውጥና በሌሎች ጉዳዮች በጋራ ለመስራትና ጠንካራ ትብብር ለመፍጠር መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል።
የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው በመሆኑ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ላይ ውጤታማ ዘመቻ ማከናወን ያስችላል ብለዋል።