ኢትዮጵያና ስፔን የአምስት ዓመት የኢኮኖሚ ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ስፔን የአምስት ዓመት የኢኮኖሚ ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 9/2015 ኢትዮጵያና ስፔን የአምስት ዓመት የኢኮኖሚ ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
ስምምነቱ ኢትዮጵያና ስፔን በቀጣይ አምስት ዓመታት የኢኮኖሚ ትብብራቸው የሚመራበት ማዕቀፍ መሆኑም ተገልጿል፡፡
የገንዘብ ሚንስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ እና የስፔን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሆሴ ማንኤል አልባሬስ ቤኖ ስምምነቱን ፈርመውታል፡፡
ኢትዮጵያና ስፔን ረጅም ጊዜ ያሰቆጠረ ግንኙነት እንዳለቸው የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ገልጸዋል፡፡
በአሁን ወቅትም የስፔን መንግስት በዓለም አቀፍ የጤና ተደራሽነት፣ በአካታች የገጠር ልማትና በስርዓተ ፆታ ዕኩልነት ለኢትዮጵያ እያበረከተ ያለውን ድጋፍ ሚኒስትሩ አድንቀዋል፡፡
ባለፋት ዓመታት የኢትዮጵያ መንግስት የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ነድፎ ዘላቂነት ያለው ፈጣን ልማት ለማምጣት፣ የግሉ ዘርፍ በየኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ተሳትፎ እንዲጎለብትና አዳዲስና ነባር የኢንቨስትንት መስኮች እንዲስፋፉ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡
የስፔን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሆሴ ማንኤል አልባሬስ ቤኖ በበኩላቸው አዲስ የተፈረመው የአምስት አመታት የትብብር ማዕቀፍ የኢትዮጵያና የስፔንን ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክር ገልጸዋል፡፡
ስፔን አለም አቀፉን ዘላቂ የልማት ግቦች ለማሳካት ከመንግስታት ጋር በትብብር በመስራት ላይ እንደምትገኝ ጠቁመዋል፡፡
አሁን የተፈረመው የትብብር ማዕቀፍም ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ በጤና፣ በገጠር ልማት፣ በስርዓተ ፆታ ዕኩልነትና በሰብዓዊ ድጋፍ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን እንደሚያጠናክር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡