ከአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 9/2015 ባለፉት ሰባት ወራት ወደ ውጭ ከተላኩት የአበባ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በግብርና ሚኒስትር የግብርና ኢንቨስትመንት ምርት ግብይት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ደረጀ አበበ፤ በዘርፉ የበጀት ዓመቱን ሰባት ወራት አፈፃፀም በተመለከተ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ አብራርተዋል።

በማብራሪያቸውም ባለፉት ሰባት ወራት ከ68 ሺህ ቶን በላይ ወደ ውጪ ከተላከ የአበባ ምርት ከ348 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡

በሌላ መልኩ 78 ሺህ ቶን የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ለውጪ ገበያ በማቅረብ ከ59 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል ብለዋል።

በመሆኑም ባለፉት ሰባት ወራት ወደ ውጭ ከተላኩት የአበባ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል።

የአበባ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶቹ ከተላኩባቸው ሀገራት መካከል ኔዘርላንድ፡ ሳኡዲ አረቢያ፣ እንግሊዝ፣ አሜሪካ፣ ኖርዌይ እና ዩናይትድ አረብ ኢምሬት ይጠቀሳሉ ብለዋል።

ከእነዚህ ምርቶች በየዓመቱ ከ500 ሺህ በላይ ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል የሚፈጠርበት መሆኑን ጠቅሰው ከዚህ በላይ የውጪ ምንዛሪ ለማግኘት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት 133 ሺህ ቶን የአበባ ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ 611 ሚሊየን ዶላር ለማግኘት መታቀዱንም ጠቁመዋል።

ከአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ደግሞ 158 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት መታቀዱንም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 60 ባለሃብቶች በአበባ ምርት ልማት ተሰማርተው በመስራት ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም