አትሌት ለሜቻ ግርማ በ3 ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር ለ25 ዓመታት ተይዞ የቆየውን ክብረወሰን በማሻሻል አሸነፈ - ኢዜአ አማርኛ
አትሌት ለሜቻ ግርማ በ3 ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር ለ25 ዓመታት ተይዞ የቆየውን ክብረወሰን በማሻሻል አሸነፈ
የካቲት 9/2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊው አትሌት ለሜቻ ግርማ በፈረንሳይ በተካሄደው የ3 ሺህ ሜትር ሩጫ ውድድር ለ25 ዓመታት ተይዞ የቆየውን ክብረወሰን በማሻሻል አሸነፈ።
የወርቅ ደረጃ የተሰጠው እ.ኤ.አ. የ2023 የፈረንሳይ ሃውትስ ዲፍራንስ አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ውድድር ተካሂዷል።
በዚህ ውድድር ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በተለያዩ ርቀቶች ድል ቀንቷቸዋል።
በውድድሩ በ3 ሺህ ሜትር ሩጫ የቶኪዮ ኦሊምፒክ የ3 ሺህ መሰናክል የብር ሜዳሊያ ባለቤት የሆነው አትሌት ለሜቻ ግርማ አዲስ የዓለም ክብረወሰን በማስመዝገብ አሸናፊ ሆኗል።
አትሌቱ 3 ሺህ ሜትሩን 7 ደቂቃ ከ23 ሰከንድ ከ81 ማይክሮ ሰከንድ በማስመዝገብ ለ25 ዓመታት ተይዞ የነበረውን ሪከርድ ጭምር በማሻሻል ነው ያሸነፈው።
በዚህም አትሌት ለሜቻ ኬንያዊው የ3 ሺህ ሜትር ንጉስ የሚባለው አትሌት ዳንኤል ኮመን ለ25 ዓመታት ይዞት የቆየውን 7 ደቂቃ 24 ሰከንድ ከ90 ማይክሮ ሰከንድ በማሻሻል ነው አዲስ ክብረወሰን ያስመዘገበው።
በሌሎች ውድድሮችም ኢትዮጵያውያን ሴት አትሌቶች ድል የቀናቸው ሲሆን፤ በሴቶች 1 ሺህ 500 ሜትር የቤት ውስጥ የሩጫ ውድድር ከአንድ እስከ አራት ተከታትለው በመግባት አሸንፈዋል።
በዚህ ውድድር በ1 ሺህ 500 ሜትር ውድድር አትሌት ጉዳፍ ፀጋዬ በአንደኝነት አጠናቃለች።
ጉዳፍን በመከተል አትሌት ሂሩት መሸሻ ሁለተኛ ስትሆን አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ እና አክሱማይት አምባዬ ሦስተኛ እና አራተኛ ሆነው ውድድሩን አጠናቀዋል።