ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ናሚቢያ በሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመስራት ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 9/2015 ኢትዮጵያ እና ናሚቢያ በሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ እና የናሚቢያ ምክትል ጠቅላይ ማኒስትርና የዓለም አቀፍ ግንኙነትና ትብብር ሚኒስትር ኔቱምቦ ናንዲ ንዳይትዋህ ተፈራርመዋል።

የናሚቢያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የዓለም አቀፍ ግንኙነትና ትብብር ሚኒስትር ኔቱምቦ ናንዲ ንዳይትዋህ በስምምነቱ ወቅት እንዳሉት የሁለቱ ሀገራት ትብብር ከናሚቢያ ከቀኝ ግዛት ነጻ መውጣት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው።

ናሚቢያ ከቅኝ ገዥዎች ነፃ በመወጣችበት ወቅት የኢትዮጵያ ተሳትፎ የጎላ እንደነበር ገልጸዋል።

ሀገራቱ በዘርፉ በስልጠና፣ በአየር መንገድ፣ ኢኮኖሚያዊ ትብብር እንዲሁም በባህል መስኮች በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን ገልጸዋል።

ስምምነቱ በኢትዮጵያ እና በናሚቢያ መካከል ጠንካራ ትብብር ለመፍጠር መሰረት የሚጥል መሆኑንም አክለዋል።

የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው በመሆኑ በቀጣናው ስራዎች ላይ ውጤታማ ዘመቻ ማከናወን ያስችላል ብለዋል።

የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ በበኩላቸው ሁለቱ ሀገራት የቆየ የዲሞክራሲ ትስስር አላቸው ብለዋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የመከላከያና የጸጥታ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ ስምምነት ተፈራርመናል ነው ያሉት።

ወታደራዊ ስልጠና በአየር ሀይል፣ ባህር ሀይልና ሌሎችም ዘርፎች የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ለማከናወን የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም