የአፍሪካን ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ለማሳለጥ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ሥምምነትን ተግባራዊ ማድረግ ወሳኝ ሚና ይጫዎታል - አምባሳደር አልበርት ሙቻንጋ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካን ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ለማሳለጥ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ሥምምነትን ተግባራዊ ማድረግ ወሳኝ ሚና ይጫዎታል - አምባሳደር አልበርት ሙቻንጋ
የካቲት 8/2015 (ኢዜአ) የአፍሪካን ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ለማሳለጥ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ሥምምነቱን ተግባራዊ ማድረግ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት በአፍሪካ ኅብረት የኢኮኖሚ ልማት፣ የንግድ ኢንዱስትሪና ማዕድን ኮሚሽነር አምባሳደር አልበርት ሙቻንጋ ተናገሩ።
ኮሚሽነሩ በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን አተገባበርን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃኝ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ ኅብረቱ ነፃ የንግድ ቀጣናን ግልጽ ራዕይና ተልዕኮ አስቀምጦ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
አገራትም የዜጎቻቸውን የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና ለሚጫወተው ነፃ የንግድ ቀጣና ተግባራዊነት በትብብር መስራት እንደሚኖርባቸው አንስተዋል።
አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናው ከካይሮ እስከ ደቡብ አፍሪካ፤ ከሞሪሺየስ እስከ ኬፕቨርዲ በአራቱም ማዕዘን የሚገኘውን ከፍተኛ የገበያ አማራጭ በመዳሰስ የአፍሪካ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን አንስተዋል።
አህጉሪቷ በአምራች ኢንዳስትሪ፣ በግብርና ምርት፣ ቱሪዝምና ትራንስፖርት፣ በትምህርትና ሥልጠና ያላትን ከፍተኛ የገበያ አማራጭ በማየት ከወጣቱ የሰው ሃይል ጋር ማገናኘት እንደሚገባም ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በትራንስፖርት ዘርፍ አፍሪካዊያንን በማስተሳሰር ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህ ብቻ በቂ ባለመሆኑ አፍሪካዊን በኢኮኖሚ የሚተሳሰሩበትን አማራጭ ማስፋት ያስፈልጋልም ብለዋል።
በነፃ የአህጉራዊ የንግድ ቀጣና ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ አቅም ያላትን አፍሪካ በመገንባት የዜጎቿን ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚስፈልግ ተናግረዋል።
የአፍሪካ አገራት መንግሥታትም ነፃ አህጉራዊ የንግድ ቀጣና ተግባራዊነት በቁርጠኝነት በመስራት የአህጉሪቱን የንግድ ትስስር ማሳለጥ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።