የደምቢዶሎ አየር ማረፊያ አማራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት የተጀመረውን ልማት ያፋጥናል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የደምቢዶሎ አየር ማረፊያ አማራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት የተጀመረውን ልማት ያፋጥናል ተባለ
ጊምቢ ግንቦት 12/2010 የደምቢዶሎ አየር ማረፊያ አማራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት የተጀመረውን ልማት ለማሳለጥ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የደምቢዶሎና አከባቢዋ ነዋሪዎች ገለፁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩን የያዘ አውሮኘላንን ጨምሮ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ቦምባርዲሮች ዛሬ ጠዋት በደምቢዶሎ አየር ማረፊያ አርፈዋል። የደምቢዶሎ ከተማ ነዋሪ አቶ መስፍን ኢዶሳ እንዳሉት በ2008 ዓ.ም አገልግሎቱን ጀምሮ ወደ አስፓልት እንዲያድግ የተደረገው የደምቢዶሎ አየር ማረፊያ ምቹ የትራንስፖርት አማራጭን በማስፋት ለእሳቸውም ሆነ ለአካባቢው ህብረተሰብ የላቀ ጠቀሜታ ይኖረዋል። አየር ማረፊያው በሀይለስላሴ ዘመነ መንግስት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ቢሆንም ካለፉት 40 ዓመታት በላይ አገልግሎት ሳይሰጥ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ ''በዚህም ምክንያት አዲስ አበባ ላይ የሚኖረንን አስቸኳይ የስራና ማህበራዊ ጉዳዮች ለማከናወን በመኪና ረዢም ርቀት መጓዝ ይጠይቀን ነበር '' ብለዋል፡፡ ''አሁን አውሮኘላን ማረፊያው በተሻለ ደረጃና ጥራት ወደ ቀድሞ አገልግሎቱ በመመለሱ ታላቅ ደስታ ተሰምቶናል'' ብለዋል። የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ደለሳ ቡልቻ በበኩላቸው በዚህ አመት የመማር ማስተማር ሂደቱን የጀመረው ደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ለተለያዩ ስልጠናዎች እንግዶችን ለመጋበዝና አብሮ ለመስራት የአየር ማረፊያው ስራ መጀመር ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል። የቴክኖሎጂ ተማሪዎች በአየር ማረፊያው ልምምድ እንዲያረጉና የተለያዩ ጥናቶችን ለማካሄድ የራሱ ድርሻ እንደሚያበረክት ገልፀው ዩኒቨርሲቲው ከኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡ ለንግድ ስራ አዲስ አበባ አንደሚመላለሱ የነገሩን ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ወንድሙ ቤዮ በጥራት የተገነባው አየር ማረፊያ የሚያደርጉትን የንግድ እንቅስቃሴ በማሳለጥ በመኪና ጉዞ የሚያጠፉትን ጊዜ በመቆጠብና ድካምን በመቀነስ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል። የአየር ማረፊያው መገንባት ለአካባቢው ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል ከመፍጠርና ለከተማዋ እድገት መፋጠን የበኩሉን አስተዋፅኦ እንደሚኖረው የገለፀው ደግሞ ወጣት ፍቃዱ ፉፋ ነው፡፡ የግንባታው ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ፍሬዘር መሃመድ በሰጡት አስተያየት አየር ማረፊያው የመጀመሪያ ደረጃ ግንባታውን 2008 ዓ.ም. አከናውኖ በመመረቅ ስራ ለጀመረው የደምቢዶሎ አውሮኘላን ማረፊያ ደረጃውን የማሳደግ ተግባር ባለፉት ሁለት ዓመታት ሲከናወን መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግንባታው ከ98 በመቶ በላይ ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል። ከ30 ሜትር በላይ ስፋትና ከሁለት ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር በላይ የማኮብኮቢያ ሜዳ ያለው ይኸው አየር ማረፊያ በአንድ ጊዜ ሁለት ቦምባርድዬር አይሮፕላኖችን የማስተናገድ አቅም እንዳለው አስታውቀዋል፡፡ የቀረው የተርሚናል፣ ትራፊክ መቆጣጠሪያ ማማና አጥር ግንባታም በጥቂት ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ጠቁመዋል። የአየር ማረፊያው ስራ አስኪያጅ አቶ በቃሉ ውለታው አየር መንገዱ በሳምንት ሶስት ቀን ዘወትር ሰኞ ረቡዕና አርብ ወደ አዲስ አበባ ቀጥታ በረራ እንደሚኖረው ገልፀዋል። ለአየር መንገዱ ግንባታ ከ176 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገ ከስራ አስኪያጁ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።