ለአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ ተሳታፊ እንግዶች የውጭ ምንዛሬን ጨምሮ ቀልጣፋ የባንክ አገልግሎቶችን እየሰጠን ነው- ባንኮች - ኢዜአ አማርኛ
ለአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ ተሳታፊ እንግዶች የውጭ ምንዛሬን ጨምሮ ቀልጣፋ የባንክ አገልግሎቶችን እየሰጠን ነው- ባንኮች
አዲስ አበባ የካቲት 08 ቀን 2015 (ኢዜአ) በአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤትና የመሪዎች ጉባኤ ለሚሳተፉ እንግዶች የውጭ ምንዛሬን ጨምሮ ሌሎች የባንክ አገልግሎቶችን በተቀላጠፈ መንገድ እየሰጡ መሆኑን ባንኮች ገለጹ፡፡
በአፍሪካ ሕብረት 36ኛው የመሪዎች ጉባኤና 42ኛው ስራ አስፈፃሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ የሚሳተፉ እንግዶች በህብረቱ ዋና መስሪያ ቤት በሚገኙ የአቢሲኒያ፣ ወጋገንና ዳሸን ባንኮች የባንክ አገልግሎት እያገኙ መሆኑን የኢዜአ ሪፖርተር ተዘዋውሮ ተመልክቷል፡፡
ከዚህም ባለፈ በሆቴሎችና በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የኤቲኤም፣ የውጭ ምንዛሬና ሌሎች የባንክ አገልግሎቶችን እየሰጡ መሆኑን ባንኮቹ ገልጸዋል።
በአቢሲኒያ ባንክ የአፍሪካ ሕብረት አገልግሎት ሲኒየር ባንኪንግ ኦፊሰር ጽዮን ሰለሞን ለኢዜአ እንዳሉት፤ እንግዶች በቆይታቸው እንደየፍላጎታቸው የውጭ ምንዛሬን ጨምሮ ሌሎች የባንክ አገልግሎቶች በተቀጣለፈ ሁኔታ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው፡
ባንኩ በአፍሪካ ሕብረት ግቢ ውስጥ፣ በአየር መንገድ፣ በሆቴሎችና በሱፐር ማርኬቶች የኤቲኤም፣ የአይቲኤምና የፖስ ማሽን አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሁሉም የውጭ ሀገር ካርዶች የውጭ ምንዛሬ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ገልጸው፤ የባንኩን አገልግሎት በምስራቅ አፍሪካ ለማስፋፋት እቅድ እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡
የወጋገን ባንክ የአፍሪካ ሕብረት ቅርንጫፍ ሱፐርቫይዘር ቃልኪዳን መርሻ ባንኩ በአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ ለሚሳተፉ እንግዶች የውጭ ምንዛሬና የጥሬ ገንዘብ አገልግሎት እየሰጠ ነው ብለዋል።
የብሔራዊ ባንክ በፈቀዳቸው የውጭ ሀገራት ገንዘቦች ኹሉ የውጭ ምንዛሬ እየተሰጠ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በዳሸን ባንክ የአፍሪካ ሕብረት ቅርንጫፍ የደንበኞች አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ ካሳሁን ኃይለማርያም በበኩላቸው በአፍሪካ ሕብረት ቅርንጫፍ ባንካቸው በኩል እንግዶችን እያስተናገዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአፍሪካ ህብረት ቅርንጫፍ ባንክ አማካኝነት በአፍሪካ ሕብረት ለሚሰሩ አፍሪካውያን የብድር አገልግሎት እየሰጡ መሆኑንም እንዲሁ።
በ42ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚዎች እና በ36ኛው የመሪዎች ጉባኤ ኢትዮ ቴሌኮምን ጨምሮ ባንኮችና ሌሎች ተቋማት ለጉባኤው ተሳታፊዎች የተለያዩ አገልግሎቶችን እየሰጡ ይገኛል።