ቀጥታ፡

አገር አቀፍ የታዳሽ ኃይል ቆጣቢ ቴክኖሎጂ ውጤቶች አውደ-ርዕይ በአዲስ አበባ ተከፈተ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 8/2015 አገር አቀፍ የታዳሽ ኃይል ቆጣቢ ቴክኖሎጂ ውጤቶች አውደ-ርዕይ እና አውደ-ጥናት በአዲስ አበባ ተከፈተ ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከልማት አጋሮች ጋር በጋራ ያዘጋጀው "የገጠር ኢነርጂ ቴክኖሎጂዎችን በጋራ እናነቃቃ" በሚል መሪ ሀሳብ ከየካቲት 8 እስከ 10 ቀን 2015 ዓ.ም ይካሄዳል።

ለሦስት ቀናት በሚቆየው አውደ-ርዕይ መክፈቻ ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ፤ የልማት ድርጅቶቹ ኃላፊዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

በአውደ-ርዕዩ ላይ የታዳሽ ኃይል ምርቶች፣ የኃይል ቆጣቢ ቴክኖሎጂ ውጤቶች ቀርበዋል።

አውደ-ርዕዩ በታዳሽ ኃይል የሶላር፣ ባዮ ኢነርጂ፣ የኃይል ቆጣቢ እና ንጹህ የማብሰያ ቴክኖሎጂዎችን የማስተዋወቅ ዓላማ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚሁ ወቅት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ፤ የኃይል አቅርቦትን ለሕብረተሰቡ ለማዳረስ በመንግሥት ብቻ ይቀርብ የነበረው አሁን የግሉ ዘርፍ እንዲያቀርብ የፖሊሲ ማሻሻያ እየተደረገ ይገኛልም ብለዋል።

በዚህም በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት የኃይል አቅርቦትን ለሕዝቡ ለማዳረስ አዋጅ መዘጋጀቱንና በዚህም የውጭ ባለሀብቶች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ሁኔታዎች እየተመቻቸ መሆኑን ጠቁመዋል።

አሁን ላይ በኢትዮጵያ 10 በመቶ ብቻ የሆነውን ከአየር ብክለት የፀዳና ኃይል ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎች አቅርቦት ለማሻሻል ከግሉ ዘርፍ ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።

90 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የማገዶ እና ሌሎች በካይ ጋዞችን በመጠቀም ምግብ የሚያበስል ሲሆን፤ ይህንንም ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የአየር ብክለትን በማስከተል በአካባቢና በአየር ንብረት ላይ ጉዳት እያስከተለ በመሆኑ በታዳሽ ኃይል የመተካቱ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

የታዳሽና ኃይል ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎችን የማስተዋወቅ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በ2030 አብዛኛው ሕዝባችን የንጹህ ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆን ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በአውደ-ርዕዩ ላይ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ምርቶችን ያቀረቡ ግለሰቦችና ድርጅቶች በበኩላቸው፤ መድረኩ ምርታቸውን ለማስተዋወቅ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም