የውጭ አገር የስራ ስምሪት የዜጎች ክብርና ደህንነት ባስጠበቀ መልኩ በአዲስ መልክ ተግባራዊ ይደረጋል- የስራና ክህሎት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ አገር የስራ ስምሪት የዜጎች ክብርና ደህንነት ባስጠበቀ መልኩ በአዲስ መልክ ተግባራዊ ይደረጋል- የስራና ክህሎት ሚኒስቴር
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 8/2015 የውጭ አገር የስራ ስምሪት የዜጎች ክብርና ደህንነት ባስጠበቀ መልኩ በአዲስ መልክ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የስራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ ።
የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ለውጭ አገር ስራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች "አዲስ እሳቤ ለዘላቂ ጉዞ" ” በሚል ርዕስ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።
ስልጠናው በስራና ክህሎት ሚኒስቴር የሪፎርም እሳቤዎች፣ በአገር ግንባታ ሂደት ያሉ የለውጥ እንቅስቃሴዎች እንዲሁም በውጭ አገር ስራ ስምሪት ላይ ያተኮረ ነው።
በስልጠናው መክፈቻ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል እንደገለፁት፤ወደ ውጭ ለስራ ስምሪት የሚንቀሳቀሱ ዜጎች ስራቸውን በእውቀትና ክህሎት ማከናውን የሚያስችላቸውን ስልጠናዎች እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል።
በተያዘው በጀት አመት ሁለት ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የአጭር ጊዜና መደበኛ ስልጠና በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ይሰጣቸዋል።
ወደ ውጭ አገር ለስራ የሚጓዙ ዜጎች ከሚያገኙት የስራ ዕድል እና ለአገር ከሚያስገኙት የውጭ ምንዛሬ በተጨማሪ የአገራቸው አምባሳደር በመሆናቸው አቅምና ክህሎታቸውን የማሳደግ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም በውጭ አገር ለስራ የሚሰማሩ ዜጎችን መብትና የስራ ላይ ደህንነታቸው ተጠብቆላቸው ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኙ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርጋቸውን ዕውቀትና ክህሎት እንዲያገኙ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን አክለዋል።
በቅርቡ ወደ ሳውዲ አረቢያና እና ሌሎች አገራት የስራ ስምሪት ለመጀመር ዝግጅት የተጠናቀቀ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሲደረግ በቆየው ዝግጅት ውስጥ እጃቸውን በብልሹ አሰራር ውስጥ ያስገቡ 17 የሚኒስቴሩ ሰራተኞች ከስራ የታገዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የውጭ አገር የስራ ስምሪት ከሙስና የጸዳ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል በቴክኖሎጂ የታገዘ የአሰራር ስርዓት የተዘረጋ መሆኑን አብራርተዋል።
ይህም የዜጎችን ደህንነትና ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያስችል የዲጂታል ስርዓት በየትኛውም ስፍራ ሆነው አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት አሰራር ገቢራዊ መደረጉን ተናግረዋል።
የውጭ አገር የስራ ስምሪት የዜጎች ክብርና ደህንነት ባስጠበቀ መልኩ በአዲስ መልክ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
በውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ዘርፍ የተሰማሩ ኤጀንሲዎች የዜጎች ክብርና ደህንነት ባስጠበቀ መልኩ መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው ገልፀው ከዚህ አንፃር ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በስልጠናው ከ400 በላይ የሚሆኑ በውጭ አገር ሥራ ስምሪት ዘርፍ የተሰማሩ ኤጀንሲዎች ተሳታፊ ሲሆኑ ስልጠናው ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚካሄድ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።