ቀጥታ፡

ኦሮሚያ ክልል አስፈጻሚ አካላትን መልሶ ሊያደራጅ ነው

አዲስ አበባ መስከረም 25/2011 በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልል ምክር ቤት የስራ አስፈጻሚው አካላት በአዲስ ሊደራጅ መሆኑ ተገለጸ። በአዲስ አደረጃጀት የመስሪያ ቤቶች ቁጥር ማለትም በኤጀንሲ፣ በባለስልጣን በቢሮ ደረጃ የሚኖሩ መስሪያ ቤቶች ቁጥር ይቀንሳል ተብሎ ይጠበቃል። የክልሉ ምክር ቤት ስራ አስፈጻሚው አካላት መልሶ ማደራጀትን በተመለከተ በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ላይ ለመምከርም ለሰኞ አስቸኳይ ስብሰባ መጥራቱን የጨፌው ቃለ አቀባይ አቶ ሃብታሙ ደምሴ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ገልጸዋል። የጨፌ ኦሮሚያ 4ኛ ዓመት 5ኛ የስራ ዘመን 3ኛ አስቸኳይ ጉባኤ የሚካሄደው በዋናነት የክልሉን አስፈጻሚ አካላት መልሶ ለማደራጀትና ስልጣንና ኃላፊነታቸውን ለመወሰን በወጣው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ለማጽደቅ እንደሆነ ይገመታል። የከዚህ ቀደሞ የስራ አስፈጻሚው አካላት አደረጃጀት በበቂ ጥናት ላይ የተመሰረተ እንዳልሆነ ያስታወሱት አቶ ሃብታሙ፤ በርካታ መስሪያ ቤቶች ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ ተግባራትን ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል። ይህም ሆኖ በርካታ በጀት የሚፈስባቸው እነኚህ መስሪያ ቤቶች "ውጤታማነታቸው እምብዛም አይደለም" ብለዋል። በመሆኑም ይህን ችግር ለማቃለል በጥናት ላይ የተመሰረተ ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን አመልከተው፤ ምክር ቤቱ ጉዳዩ ላይ ተወያይቶ እንዲያጸድቀው አስቸኳይ ስብሰባ መጠራቱን ተናግረዋል። ረቂቅ አዋጁ የስራ አስፈጻሚ አካላት አደረጃጀቶች ከህብረተሰቡ ጋር በቅርበት እንዲያገለግሉ ከማድረግ አኳያ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም