ቀጥታ፡

የደቡብ ክልል ምክር ቤት ባለፉት ስድስት ወራት የህዝብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ስራዎችን አከናውኗል- አፈ ጉባዔዋ

ሀዋሳ ፤ የካቲት 8 ቀን 2015 (ኢዜአ)፡- የደቡብ ብሔሮች ፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ባለፉት ስድስት ወራት የህዝብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ስራዎች ማከናወኑን የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባዔ ፋጤ ሰርሞሎ አስታወቁ።

የክልሉን ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔን በንግግር የከፈቱት ዋና አፈ ጉባዔዋ ፤ የክልሉ ምከር ቤት በግማሽ በጀት ዓመቱ በመልካም አስተዳደር፣ልማትና ፍትህን ለማረጋገጥና የህዝብ ተጠቃሚነትን በማጉላት ረገድ ሰፊ ሥራዎችን ሠርቷል ብለዋል።

በክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም የህዝብ ውክልና ሥራን ጨምሮ ሰፊ ርብርብ በማድረግ አበረታች ውጤቶችን ለማስመዝገብ መቻሉንም ገልጸዋል።

በተለይ በቋሚ ኮሚቴዎች በኩል የሚደረግ የአስፈፃሚ አካላት ክትትል፣ቁጥጥርና ግምገማ ተግባር በእውቀት ችግሮችን መፍታት የሚችልና አቅጣጫ ጠቋሚ እንዲሆን ለማስቻል ልዩ ልዩ አዳዲስ አሰራሮችን መዘርጋታቸውን ጠቅሰዋል።

ከአስፈጻሚ አካላት ተግባራት አንፃር ግብርና በክልሉ እድገትን ለማረጋገጥና የምግብ ዋስትና ችግር ለመፍታት ያለው ድርሻ የጎላ በመሆኑ የዘርፉ ሥራዎችን ለማስፋፋት ተገቢ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል።

በተለይ በቅርቡ የተጀመረው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በልዩ ትኩረት መምራት ያስፈልጋል ሲሉ አፈ ጉባዔዋ ተናግረዋል።

በክልሉ በዝናብ እጥረትና መቆራረጥ ምክንያት የሰውና እንስሳት የአደጋ ተጋላጭነት እየጨመረ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህንን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተቋቋመው ግብረ ኃይል የጀመራቸው የቅድመ መከላከልና የማስጠንቀቅና ድጋፍ የመስጠት ስራዎች በተቀመጠው አቅጣጫ ተጠናክረው እንዲቀጥሉም አመልክተዋል።

የምክር ቤቱ ጉባዔም በክልሉ ታሪካዊ ህዝበ ውሳኔ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ተደርጎ ውጤት እየተጠባበቅን ባለንበት ወቅት መካሄዱ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

ለምርጫው ሂደት ስኬታማነት የበኩላቸውን ሚና ለተጫወቱ አካላትና ለመላው የክልሉ ህዝብ በምክር ቤቱ ስም ምስጋና አቅርበዋል።

ጉባዔው በሁለት ቀናት ቆይታው በልዩ ልዩ አጀንዳዎች ላይ በመወያየት ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።

ዛሬ ጥዋት የተጀመረው ጉባዔው የክልሉ ምክር ቤት ስድስተኛ ዙር አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ረቂቅ ቃለ ጉባኤን አጽድቋል።

በአሁኑ ወቅት የክልሉ መንግስት የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው እየቀረበ ይገኛል።

በጉባዔው ላይ የምክር ቤቱ አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም