በንግስት እሌኒ መሐመድ መታሰቢያ ሆስፒታል ተገቢ የካርድ አገልግሎት እያገኙ አለመሆናቸውን ታካሚዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
በንግስት እሌኒ መሐመድ መታሰቢያ ሆስፒታል ተገቢ የካርድ አገልግሎት እያገኙ አለመሆናቸውን ታካሚዎች ገለጹ
ሆሳዕና መስከረም 25/2011 በዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ የንግስት እሌኒ መሐመድ መታሰቢያ ሆስፒታል ታካሚዎች በካርድ ክፍል ፈጣንና ተገቢ አገልግሎት እያገኙ አለመሆናቸውን ገለጹ፡፡ የሆስፒታሉ አስተዳደር በበኩሉ ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የሆስፒታሉ ተገልጋዮች እንዳሉት ከካርድ አገልግሎት ጋር በተያያዘ እንግልት እየደረሰባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከሀድያ ዞን ሶሮ ወረዳ ለህክምና ወደ ሆስፒታሉ የመጡት አቶ ተስፋዬ ፈለቀ በሆስፒታሉ በጠዋት ተገኝተው ለመታከም ቢሞክሩም ቀደም ሲል የታከሙበት ካርድ ተፈልጎ ባለመገኘቱ ህክምና ለማግኘት መጉላላታቸውን ተናግረዋል፡፡ በእዚህም ህክምና ለማግኘት አዲስ ካርድ ለማውጣት መገደዳቸውን የገለጹት አቶ ተስፋዬ አፈጣኝ ህክምና ለሚሹ ህመሞች ፈጣን የካርድ አገልግሎት ለማግኘት የማይቻልበት ሁኔታ እንዳለም ማስተዋላቸውን ተናግረዋል፡፡ በሀድያ ዞን የሊች አምባ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አየለች ፈለቀ በበኩላቸው " የሆስፒታሉ የካርድ ክፍል ሠራተኞች ለተካሚዎች ፈጣን ተገቢ አገልግሎት ከመስጠት አንጻር የጎላ ችግር አለባቸው" ብለዋል ፡፡ የክፍሉ ሠራተኞች ለሚያውቁት ታካሚ ቅድሚያ እንደሚሰጡና በእዚህም ለሕክምና ተራ የሚጠብቀውን ተገልጋይ ለእንግልት እየዳረጉት መሆኑን ተናግረዋል። በሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ጃሎ ናረሞ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ አበራ አባይነህ በበኩላቸው ልጃቸው በጠና ታሞ ወደሆስፒታሉ ቢመጡም በካርድ ክፍል መስተጓጎል እንዳጋጠማቸው አስረድተዋል። የልጃቸው ካርድ ተፈልጎ በመታጣቱ ምክንያት ያለህክምና ለሰዓታት መቆየታቸውን የገለጹት አቶ አበራ፣ በካርድ ክፍል ሠራተኞች ላይ የቀናነትና የስነምግባር ችግር እንዳለ መታዘባቸውንም ገልጸዋል። በቀጣይ ተገልጋዩ ህብረተሰብ የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኝ ሆስፒታሉ በእዚህ ረገድ ያለበትን ችግር ፈጥኖ እንዲፈታም ጠይቀዋል። በዋቻሞ ዩንቨርሲቲ ንግስት ህሌኒ መሐመድ መታሰቢያ ሆስፒታል ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር አያኖ ሻንቆ በተገልጋዮች የተነሱት ችግሮች ትክክል መሆናቸውን አምነው በሆስፒታሉ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሆስፒታሉ ረዥም ጊዜ በማስቆጠሩና ከታካሚው ብዛት ጋር የሚመጣጠን የቅድመ ዝግጅት ሥራ ባለመሰራቱ ለችግሩ መፈጠር አንድ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ታካሚዎች በድንገተኛ አደጋ ለሕክምና በሚመጡበት ወቅት ተገቢውን መረጃ የማይሰጡበት ሁኔታ እንዳለና ይህም በድጋሚ ለህክምና ሲመጡ ከሚሰጡት መረጃ ጋር ካልተጣጣመ ካርዳቸው የሚጠፋበት ሁኔታ እንደሚኖር አስረድተዋል። ከካርድ ክፍል ጋር በተያያዘ ከተገልጋዮች የተነሳውን ቅሬታ ለመፍታት ድርጊቱን ሲፈጽሙ ለነበሩ የክፍሉ ሠራተኞች የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንዲደርሳቸው መደረጉን ገልጸዋል። በተጨማሪም በአንድ መስኮት ብቻ ይሰጥ የነበረውን የካርድ አገልግሎት በሁለት መስኮቶች እንዲሰጥ መደረጉን ነው የተናገሩት። የታካሚዎችን እንግልት ለማስቀረትና ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ለማድረግ በቅርቡ በሆስፒታሉ በኤሌክትሮኒክሰ የታገዘ የካርድ አገልግሎት ሥራ እንደሚጀመር ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡ በሆስፒታሉ ካርድ ክፍል አገልግሎት ለማግኘት ረጅም ሰልፎች መጠበቅ ግድ መሆኑን በስፍራው የተገኘው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር ተመልክቷል፡፡