ለአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ የሚመጡ እንግዶችን በተለመደው ኢትዮጵያዊ እንግዳ ተቀባይነት ተቀብሎ መሸኘት ይገባል- አምባሳደር ብርቱካን አያኖ - ኢዜአ አማርኛ
ለአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ የሚመጡ እንግዶችን በተለመደው ኢትዮጵያዊ እንግዳ ተቀባይነት ተቀብሎ መሸኘት ይገባል- አምባሳደር ብርቱካን አያኖ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 7/2015 ለአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ የሚመጡ እንግዶችን በተለመደው ኢትዮጵያዊ እንግዳ ተቀባይነት ተቀብሎ መሸኘት እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገለጹ።
በ42ኛው የአፍሪካ ኅብረት የአስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የሚሳተፉ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አዲስ አበባ በመግባት ላይ ይገኛሉ።
የአገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የተመራው ልዑካን ቡድን ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ 42ኛው የአፍሪካ ኅብረት የአስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባና ለ36ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤና በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል።
ዝግጅቱ ኮሚቴ ተዋቅሮ በሁሉም ዘርፍ በቂና አስፈላጊ የተባለ ዝግጅት መደረጉን አክለዋል።
በዚህ መሰረት በ42ኛው የአፍሪካ ህብረት የአስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የሚሳተፉ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አብዛኛዎቹ አዲስ አበባ መግባታቸውን ተናግረዋል።
በመጪው ቅዳሜና እሁድ በሚካሄደው 36ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ የበርካታ አፍሪካ አገራት መሪዎች በስብሰባው እንደሚገኙ ማረጋገጣቸውንም ነው የገለጹት።
ለአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ የሚመጡ እንግዶችን በተለመደው ኢትዮጵያዊ እንግዳ ተቀባይነት በጥሩ መስተንግዶ ተቀብሎ መሸኘት እንደሚገባ አሳስበዋል።
እንግዶችን በጥሩ ሁኔታ ተቀብሎ በማስተናገድ የኢትዮጵያን ገጽታ መገንባት እንደሚገባም ተናግረዋል።