ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካ ሠላምና መረጋጋት የምታደርገውን አስተዋጽኦ አጠናክራ ትቀጥላለች

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 7/2015 ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካ ሠላምና መረጋጋት የምታደርገውን አስተዋጽኦ አጠናክራ እንደምትቀጥል የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ ተናገሩ።

በአዲስ አበባ ላለፉት አምስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው 31ኛው የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ዛሬ በተካሄደው የመከላከያና ጸጥታ ሚኒስትሮች ኮሚቴ ስብሰባ ተጠናቋል።

ዶክተር አብርሃም በላይ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የጸጥታ ሁኔታዎች በፍጥነት በሚቀያየርበት ምስራቅ አፍሪካ አካባቢ የተጠናከረ የጋራ ሃይል ያስፈልጋል።

በቀጣናው የሚፈጠሩ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት፣ የጋራ አቅም ለመፍጠር፣ ተቋሙን ማጠናከርና መሰል ጉዳዮች ላይ የመከላከያና ጸጥታ ሚኒስትሮች ኮሚቴ ውይይት ማድረጉን አብራርተዋል።

ጠንካራ የተጠባባቂ ኃይል ተቋምን ለመፍጠር እስካሁን አባል ያልሆኑ አገራት አባል በሚሆኑባቸው ሁኔታዎች ላይም መመከሩን ጠቁመዋል።

"የምስራቅ አፍሪካ ችግሮች መፈታት ያለባቸው በራሳችን ነው" ያሉት ዶክተር አብርሃም የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይልን በማጠናከር የሚፈጠሩ ችግሮችን በጋራ መፍታት እንደሚቻል ነው ያብራሩት።

ለዚህም ኢትዮጵያ ቀደም ሲል በቀጠናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ስታደርግ የነበረውን አስተዋጽኦ አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሃይል አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ጌታቸው ሽፈራው በበኩላቸው ስብሰባው ተቋሙን የበለጠ የሚያጠናክሩ ጠቃሚ ሃሳቦች እንደተነሱበት ገልጸዋል።

የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሃይል የተሟላ ግዳጅ ለመፈጸም የሚያስችል ቁመናን መገንባት መቻሉን ገልጸዋል።

ጎን ለጎንም አባል አገራቱ በቀጣይ የፋይናንስ ድጋፋቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የ2022 ተጠባባቂ ኃይሉን በሊቀ-መንበርነት በመራችበት ወቅት ውጤታማ ሥራዎችን ማከናወኗን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ሊቀ-መንበርነቷን ለኬንያ አስረክባለች።

የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ከተመሰረተ 20 ዓመታትን አስቆጥሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም