ኢትዮጵያና ኡጋንዳ በመከላከያ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ይሰራሉ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 7/2015 ኢትዮጵያና ኡጋንዳ በመከላከያ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰሩ የአገራቱ የመከላከያ ሚኒስትሮች ገለጹ።

የሁለቱ አገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች በአዲስ አበባ በተካሄደው 31ኛው የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል የመከላከያና ጸጥታ ሚኒስትሮች ኮሚቴ ስብሰባ ጎን ለጎን ተወያይተዋል። 

በውይይታቸው ሁለቱ አገሮች በሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ ትብብራቸውን በማጠናከር በሁለትዮሽ እንዲሁም በቀጣናው መሥራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ መምክረዋል።

የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ ከውይይቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ፤ ኢትዮጵያ ከኡጋንዳ ጋር በመከላከያ ዘርፍ በትብብር የሚሰሩበት ሥምምነት አለ ብለዋል። 

ሁለቱ አገራት ያደረጉትን ሥምምነት የበለጠ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መግባባታቸውን ገልጸዋል። 

አጠቃላይ ወታደራዊ ትብብርን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሚያስችል ውይይት መደረጉን ተናግረዋል። 

የኡጋንዳ መከላከያ ጉዳዮች ሚኒስትር ቪሲንቲ ሴቢቻ በበኩላቸው ኡጋንዳ በሰላምና ጸጥታ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር የበለጠ ማጠናከር ትፈልጋለች። 

ሁለቱ አገራት ቀደም ሲል የነበራቸውን የመከላከያ ሥምምነት ትብብር ማየትና መከለስ የውይይታቸው አንደኛው ጉዳይ እንደነበር ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም