ቀጥታ፡

የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ዘርፍ የጀመረችውን ቀጣናዊ ትስስር የምታጠናክርበት ነው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 7/2015 የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የጀመረችውን ቀጣናዊ ትስስር ይበልጥ የምታጠናክርበት እንደሚሆን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ፡፡

የ36ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ "የአፍሪካን ነፃ የንግድ ቀጣና ትግበራ ማፋጠን" በሚል መሪ ሀሳብ መካሄዱ ኢትዮጵያ ያላትን ምቹ የንግድና ኢንቨስትመንት አማራጮች በስፋት ለማስተዋወቅ ያግዛል ተብሏል፡፡  

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት ገጽታ ለዓለም ማስተዋወቅ የተቋሙ ቀዳሚ ተግባር ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሀገራት ጋር ያላትን ትስስር በማጠናከር ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻነቷን ማረጋገጥ የሚያስችል እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ 

የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና በአፍሪካውያን መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር የሚያጎለብት በመሆኑ የዘንድሮውን የህብረቱን ጉባኤ የኢትዮጵያን ገፅታ ለማስተዋወቅ እንጠቀምበታለን ብለዋል፡፡ 

ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የኢትዮጵያ ምርቶችንና የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማየት የጅቡቲና ኬንያ የቢዝነስ ልዑካን ወደ ኢትዮጵየ መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያን ገፅታ ለዓለም በማስተዋወቅ ምቹና ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግም የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ትግበራን በባለቤትነት የማከናወን ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል፡፡ 

በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ የሚመጡ ባለሃብቶችም ያለውን ምቹ ሁኔታ ተረድተው በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ትኩረት መስጠታቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት ገጽታ ለማስተዋወቅና የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ከአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በተጨማሪ በመጭው ሚያዚያ ወር "ኢንቨስት ኢን ኢትዮጵያ" የተሰኘ መርሀ-ግብር ይዘጋጃልም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም