የእጣንና ሙጫ ምርት ሽያጭ ከ163 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ ነው--የምዕራብ ጎንደር ዞን - ኢዜአ አማርኛ
የእጣንና ሙጫ ምርት ሽያጭ ከ163 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ ነው--የምዕራብ ጎንደር ዞን

መተማ (ኢዜአ) የካቲት 7/2015 በምዕራብ ጎንደር ዞን ዘንድሮ ለገበያ ከሚቀርብ የእጣንና ሙጫ ምርት ሽያጭ ከ163 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ደንና ዱር እንስሳት አካባቢ ጥበቃ መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው ደንና እና አካባቢ ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ሀብታሙ አድጎ ለኢዜአ እንደገለጹት ገቢውን ለማግኘት የታቀደው 9 ሺህ 200 ኩንታል የእጣንና ሙጫ ምርት ለገበያ በማቅረብ ነው።

በዞኑ ሰፊ የእጣንና ሙጫ ምርት መሰብሰብ የሚያስችል አቅም እንዳለ ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት 6 ሺህ 300 ኩንታል የእጣን እና 2 ሺህ 900 ኩንታል የሙጫ ምርት የመሰብሰብ ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
እስካሁን ከ1 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡንና ከምርት ሽያጭም ከ163 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
ከዞኑ አምና ወደ 4 ሺህ 800 ኩንታል የሚጠጋ የእጣንና ሙጫ ለገበያ ቀርቦ 67 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን አስታውሰዋል።

ህገ-ወጥ የእጣንና ሙጫ የማምረት ሂደትን እና ደኑን ከጥፋት ለመታደግ በየወረዳው የደን ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ የክትትልና የቁጥጥር ስራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በዞኑ ምርቱ በብዛት በሚገኝባቸው ወረዳዎች የደንና ደን ውጤቶች ኬላ በማጠናከር ህገ ወጦችን ለሕግ የማቅረብ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
በምዕራብ ጎንደር ዞን ከ40 ሺህ ኩንታል በላይ የእጣንና ሙጫ ምርት ማግኘት የሚያስችል ሀብት መኖሩን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።