ቀጥታ፡

በአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ የኃይል መቆራረጥ እንዳይፈጠር በቂ ዝግጅት ተደርጓል

የካቲት (ኢዜአ) 7/2015 በአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ እንዳይፈጠር በቂ ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ከተማ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለጸ።

የአዲስ አበባ ከተማ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ በቀለ ክፍሌ ለኢዜአ እንደገለጹት በአፍሪካ ኅብረት 42ኛው አስፈፃሚ ስብሰባና በ36ኛው የመሪዎች ጉባኤ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ እንዳይፈጠር በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

የአፍሪካ ኅብረት ከነገ ጀምሮ በሚያካሂደው የሥራ አስፈፃሚ ስብሰባና መሪዎች ጉባኤ ለመሳተፍ የመጡ እንግዶች በሚያርፉባቸው ሆቴሎች አካባቢ የሚገኙ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ በቂ ጥገና መደረጉን አስታውቀዋል።

በኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ከተደረገው የጥገና ሥራ በተጨማሪም ከባለ አንድ እስከ አምስት ኮከብ ደረጃ ያላቸው 81 ሆቴሎች የኃይል ማስተላለፊያ ጄኔሬተራቸውን በመፈተሽ ዝግጁ እንዲሆኑ መደረጉን ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት ኅብረቱ ባካሄደው ስብሰባ ወቅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዝርዝር በሰጣቸው 76 ሆቴሎች በቂ ዝግጅት በማድረግ ያልምንም ኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ መጠናቀቁን አስታውሰዋል።

በዘንድሮው የሥራ አስፈፃሚ ስብሰባና የመሪዎች ጉባኤም 81 በሚሆኑ ሆቴሎች ላይ የኃይል መቆራረጥ እንዳይፈጠር በቂ ቅድመ ዝግጅት ስራ መሰራቱን አስረድተዋል።

በአፍሪካ ኅብረት መሰብሰቢያ አዳራሽም የኃይል መቆራረጥ እንዳይፈጠር በመዲናዋ ከሚገኘው የሜክሲኮ የማከፋፈያ ጣቢያ በአንድ መስመር ቀጥታ ኃይል እንዲያገኝ ተደርጓል ብለዋል።

የኃይል መቆራረጥ የሚፈጠርበት አጋጣሚ ካለም ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የተቋሙን ሰራተኞች ምደባ በማድረግ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።

ለኅብረቱ የሥራ አስፈፃሚ ስብሰባና የመሪዎች ጉባኤ የሚመጡ እንግዶች ይንቀሳቀሱባቸዋል ተብለው በሚታሰቡ አካባቢዎችም የውስጥ ለውስጥ ጥገና መደረጉን አንስተዋል።

ኅብረተሰቡም ብልሽት የሚያጋጥማቸውን የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን ሲያስተውል በ095 ነፃ የስልክ መስመር በመደወል ለተቋሙ ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም