በዋግህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በአስከተማ የተቋረጠው የኤሌክትሪክ ሀይል በመጀመሩ የሀይል አቅርቦት ችግራቸው መፈታቱን የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
በዋግህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በአስከተማ የተቋረጠው የኤሌክትሪክ ሀይል በመጀመሩ የሀይል አቅርቦት ችግራቸው መፈታቱን የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ

ሰቆጣ (ኢዜአ) የካቲት 7/2015 በዋግህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በአስከተማ የተቋረጠው የኤሌክትሪክ ሀይል በመጀመሩ የሀይል አቅርቦት ችግራቸው መፈታቱን የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።
በአስተዳደሩ ጋዝጊብላ ወረዳ የአስከተማ ነዋሪ ወጣት ወልደሰንበት እጅጉ ለኢዜአ እንደገለፀው፣ በከተማው የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቋረጡ ሥራው ላይ ጫና ፈጥሮበት ቆይቷል።
በኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት ችግር ምክንያት የኤሌክትሮኒክስ ጥገና ሥራውን እስከማቆም ደርሶ እንደነበርም ተናግሯል።
በአሁኑ ወቅት በከተማው ከሁለት ዓመት በላይ ተቋርጦ የነበረው የኤሌክትሪክ አገልግሎት መጀመሩ የኤሌክትሮኒክስ ጥገና ስራውን ዳግም መጀመሩን ገልጿል።
በከተማው በወንዶች የውበት ሳሎን ሥራ የተሰማሩት አቶ ዮሴፍ አጥናፉ በበኩላቸው፣ የመብራት አቅርቦት መቋረጡ ለወጭና ለእንግልት ዳርጓቸው እንደነበር ተናግረዋል።
የውበት ሳሎኑ ሥራ እንዳይቋረጥ ከ40 ሺህ ብር በላይ ወጭ በማድረግ ጀነሬተር ለመግዛት መገደዳቸውን ጠቁመው፣ ለጀነሬተር ናፍጣ በበቂ ሁኔታ አለመገኘቱ በስራቸው ላይ ችግር መፍጠሩንም አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅት በከተማው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ዳግም መጀመሩ እንዳስደሰታቸው የገለጹት አቶ ዮሴፍ፣ "የኤሌክትሪክ ሃይል ማግኘታችን የጨለማ ኑሮን እንደመላቀቅ ይቆጠራል" ብለዋል።
"የኤሌክትሪክ ሃይል መቋረጡ በተለይ ለእናቶች ፈተና ነበር" ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ፋንታይቱ ጥጋቡ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ ናቸው።
የኤሌክትሪክ ሃይል በመቋረጡ በናፍጣ ወፍጮ እህል ለማስፈጨት ቀደም ሲል ከሚከፍሉት በሁለት እጥፍ ዋጋ ይጠየቁ እንደነበር አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅት በከተማቸው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ዳግም መጀመሩ ይህን የዋጋ ጭማሪ ከማስቀረት በላይ እናቶችን ከጭስ ስለሚያላቅቅ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሰቆጣ የደንበኞች አገልግሎት መስጫ ማዕከል ሥራ አስኪያጅ አቶ ኪሮስ ፈረደ በበኩላቸው፣ በጦርነቱ በኤሌክትርክ መሰረተ ልማት ላይ በደረሰ ጉዳት አስከተማና አካባቢው ከሁለት ዓመታት በላይ ከሀይል እቅርቦት ውጪ ሆነው መቆየታቸውን ተናግረዋል።

አገልግሎቱን መልሶ ለማስጀመር ከሰቆጣ የሃይል ማከፋፈያ ጀምሮ እስከ አስከተማ ድረስ 42 ኪሎ ሜትር የሃይል ማስተላለፊያ ምሰሶዎች ላይ የጥገና ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።
በጥገና ሥራውም የአስከተማን ጨምሮ ወለህ፣ ቲያ እና ዛሮታ ቀበሌዎች ከትናንት ጀምሮ የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በብሔረሰብ አስተዳደሩ በጦርነቱ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የኤሌክትሪክ አገልግሎት በተከናወነ የጥገና ሥራ በርካታ አካባቢዎች ዳግም አገልግሎት ማግኘታቸውን አቶ ኪሮስ ገልጸዋል።