የአሜሪካ መንግሥት ዓለም አቀፍ የኤድስ መርኃ-ግብር ለኢትዮጵያ ጤናው ዘርፍ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የአሜሪካ መንግሥት ዓለም አቀፍ የኤድስ መርኃ-ግብር ለኢትዮጵያ ጤናው ዘርፍ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 7/2015 የአሜሪካ መንግሥት ዓለም አቀፍ የኤድስ መርኃ-ግብር በኢትዮጵያ በጤና ዘርፍ የሚያደርገውን ዘርፈ ብዙ ድጋፎች አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ።
የአሜሪካ መንግሥት ዓለም አቀፍ የኤድስ መርኃ-ግብር አስተባባሪና በጤናው ዘርፍ ዲፕሎማሲ ልዩ ተወካይ የተመራ ልዑክ ዛሬ የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎትን ጎብኝቷል።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የሕክምና ግብዓቶች ድጋፍ በምን መልኩ ተረክቦ ወደ ኅብረተሰቡ እንደሚያደርስ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት 30 በመቶ የሚሆነውን የመድኃኒትና የህክምና ግብዓቶችን ወደ ጤና ተቋማት የማድረስ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በጤና ዘርፉ እያንዳንዱ የጤና አገልግሎት ላይ የሚሰራው ሥራ ያለ ግብዓት ማስፈጸም አይቻልም ያሉት ዳይሬክተሩ ለዚህም፣ እየተደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በተለይም የአሜሪካ መንግሥት ዓለም አቀፍ የኤድስ መርኃ-ግብር አስተባባሪ በኢትዮጵያ ላለፉት በርካታ አመታት፣ በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ቲቢና ወባን ለመግታት ትልቅ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
በቀጣይም ይህ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ነው ጥሪ ያቀረቡት።
በቀጣይም የአሜሪካ መንግሥት ዓለም አቀፍ የኤድስ መርኃ ግብርና ድጋፍ ሰጪ አካላት አገልግሎቱ የተሳካ እንዲሆን የተሽከርካሪና ሌሎችም ድጋፎች እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ከአጋር አካላት በሚቀርቡ ድጋፎች 30 በመቶ የሆነውን የቀጥታ የመድኃኒትና የሕክምና ግብዓቶች ሥርጭት ወደ 50 በመቶ ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የአሜሪካ መንግሥት ዓለም አቀፍ የኤድስ መርኃ-ግብር አስተባባሪና የጤናው ዘርፍ ዲፕሎማሲ ልዩ ተወካይ ዶክተር ጆን ኪንጋሶንግ በበኩላቸው፣ ለመድኃኒት አቅርቦት ሥራ ጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
አገልግሎቱ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከ14 ቢሊየን ብር በላይ የሚተመን መድኃኒቶችንና የህክምና መሳሪያዎችን ለመንግሥት የጤና ተቋማት ማሰራጨት መቻሉን ገልጸዋል።
ከዚህም ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው በአጋር አካላት ድጋፍ የተከናወነ መሆኑን ተገልጿል።