የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ኢትዮጵያ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና የተሻለ የገበያ ድርሻ እንዲኖራት እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ኢትዮጵያ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና የተሻለ የገበያ ድርሻ እንዲኖራት እየሰራ ነው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 7/2015 ኢትዮጵያ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና የተሻለ የገበያ ድርሻ እንዲኖራት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።
የንግዱ ማኅበረሰብ እንደ አገር በአፍሪካ ገበያ ተወዳዳሪና ተፈላጊ ምርቶችን ለማቅረብ የራሱን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ እንዳለው መኮንን፤ አንድ ገበያ የመሰረቱ አገራት ውጤታማ ስለመሆናቸው የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራትን ለአብነት አንስተዋል።
የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና በዓለም ላይ ከፍተኛ ግብይት የሚፈጸምበት እንደሚሆን ገልጸው፤ ስምምነቱ በ2063 አንድ አህጉራዊ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት የተያዘውን ግብ ስኬታማ ሚና እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ስምምነቱን ከመፈረምና ከማጽደቅ ባሻገር ለትግበራው ዝርዝር መንደርደሪያ ነጥቦችን ማቅረቧን እና ለገቢራዊነቱም ቁርጠኛ ዝግጅት እያደረገች መሆኑን አንስተዋል።
ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነቱ ሰፊ ሀብትና ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ ከጎረቤትም ሆነ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር የሚኖራትን የውጭ ገበያ ንግድ ለማሳለጥ፣ በሰዎች ነፃ ዝውውርና የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ በነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት መሰረት በየትኛውም የአፍሪካ ገበያ ተቀባይነት እንዲኖራት ተወዳዳሪና ተመራጭነቷን ለማሳደግ የሚያስችሉ ምርትና ምርታማነት እንዲሁም ጥራት ማረጋገጥ ላይ በትኩረት እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።
የምርት ጥራት ተቆጣጣሪ ተቋማትን ማጠናከር፣ የላኪና አስመጪዎችን ተሳትፎ በማሳደግ የአገራዊ ኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያነሱት።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ የገበያ ድርሻ እንዲኖራት የሚያስችሉ የውጭ ንግድ መጠን እና የምርት አቅምን ማጎልበት እንዲሁም በምርት ጥራት ላይ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከኮቪድና ድኅረ-ኮቪድ በተከሰቱ ዓለም አቀፋዊ ችግሮች የተፈተነ ቢሆንም ተፅዕኖውን ተቋቁሞ እየተሻገረ መሆኑን የስንዴ ምርትን ለማሳያነት ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል የተዛባ የንግድ ሚዛንን ለማስተካከል ተወዳዳሪ የሚያደርጉ አዳዲስ ምርቶችን ወደ ውጭ ገበያ ማስገባትና የገበያ መዳረሻዎችን ማስፋት ላይ ልዩ ትኩረት ተድርጎ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የአፍሪካ አህጉራዊ የነፃ ንግድ ቀጣና በዕውቀትና በጥበብ የሚገባበት በመሆኑ፤ የንግዱ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያን እንደ አገር ተወዳዳሪ በሚያደርጉ ሥራዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባ ገልጸዋል።
በተለይም አስመጪና ላኪዎች በተግባር ለውጤት የሚያበቁ ጥረቶች እንደሚጠበቁባቸው ነው ጥሪ ያቀረቡት።
ከአምስት ዓመታት በፊት በተደረገው የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት 54 ሀገራት ስምምነቱን ተቀብለው ፈርመዋል።
ነገ ጀምሮ በሚደረገው የአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ ዐቢይ ትኩረትና የመሪ ቃሉ ሃሳብ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና መሆኑ ይታወቃል።