በሲዳማ ክልል የፀሐይ ኃይልን በመጠቀም ከ30ሺ በላይ ለሆኑ ነዋሪዎች የንጹህ መጠጥ ውኃ ተደራሽ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል የፀሐይ ኃይልን በመጠቀም ከ30ሺ በላይ ለሆኑ ነዋሪዎች የንጹህ መጠጥ ውኃ ተደራሽ እየተደረገ ነው
ሀዋሳ የካቲት 07 ቀን 2015 (ኢዜአ) በሲዳማ ክልል የፀሐይ ኃይልን በመጠቀም ከ30ሺ በላይ ለሆኑ ነዋሪዎች የንጹህ የመጠጥ ውኃ ተደራሽ ማድረግ መቻሉን የክልሉ የውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ገለጸ።
በክልሉ በፀሐይ ኃይል በሚሰሩ የሶላር ሲይስተሞች በመጠቀም ለነዳጅ ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ ገንዘብ ማስቀረት መቻሉም ተገልጿል።
የሲዳማ ክልል የውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ውብሸት ጸጋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አገልግሎቱ በተጀመረባቸው ወረዳዎች የውኃ አቅርቦቱን ያለማቆራረጥ ማድረስ መቻሉን ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም ለዜጎች ንጹህ ውሃ ተደራሽ ለማድረግ የነዳጅ ዋጋ መናር ፈተና እንደነበር አስታውሰው፣ በሶላር ኢነርጂ አገልግሎቱ በተጀመረበት አከባቢ ችግሩ በመሰረታዊነት መፈታቱን ተናግረዋል።
ከተለያዩ አካላት በተገኙ ድጋፎች በወንዶ ገነት ወረዳ ስምንት ቀበሌዎች እንዲሁም በሎካ አባያ ወረዳም ከ26ሺ በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደረጉ ሁለት ፕሮጀክቶች ተገንብተው በአገልግሎት ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በቀጣይም በሁሉም የክልሉ ወረዳዎች ይህን የሶላር ኢነርጂ በማዳረስ የንጹህ መጠጥ ውሃን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
በሲዳማ ክልል የወንዶ ገነት ወረዳ የውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሳይ ዘነበ በበኩላቸው፤ በወረዳቸው ለስምንት ቀበሌ ነዋሪዎች ሶላር ኢነርጂን በመጠቀም የንጹህ መጠጥ ውሃ ማቅረበ መቻሉን ገልጸዋል።
ቴክኖሎጂው አዋጭ፣ ውጤታማና በርካቶችን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በወንዶ ገነት ወረዳ ዮዎ ቀበሌ በቴክሎጂው አማካኝነት የንጹህ መጠጥ ውሃ ያገኙ አርሶ አደሮች በሰጡት አስተያየት ንጹህ መጠጥ ውሃን ማግኘት ከጀመሩ አንድ ዓመት መቆጠሩን ገልጸዋል።
ከዚያ በፊት ረጅም ርቀት በመጓዝ የወንዝ ውሃን ሲቀዱ እንደነበር ገልጸው፣ አሁን ላይ ችግራቸው ሙሉ በሙሉ መቀረፉን ተናግረዋል።
በሲዳማ ክልል የተለያዩ የሃይል አማራጮችን በመጠቀም ለዜጎች የተለያዩ አገልግሎቶች እየተሰጠ ሲሆን ከዚህም ውስጥ በበርካታ የገጠር ቀበሌዎች በፀሐይ ሃይል የሚሰሩ አትክልትና ፍራፍሬን ለማቀዝቀዝ የሚውሉ መሳሪያዎች ተገጥመዋል።