ቀጥታ፡

በሚቀጥሉት አስር ቀናት የተወሰኑ የአገሪቱ አካባቢዎች የበልግ ዝናብ እንደሚያገኙ የሚቲዎሮሎጂ ትንበያ አመላከተ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 7/2015 ከያዝነው ሳምንት ጀምሮ በሚቀጥሉት አስር ቀናት የተወሰኑ የአገሪቱ አካባቢዎች የበልግ ዝናብ እንደሚያገኙ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስትቲዩት ገለጸ።

ኢንስትቲዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ፤ በሚቀጥሉት አስር ቀናት በተወሰኑ አካባቢዎች የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች ላይ መጠነኛ ዝናብ ይኖራል ብሏል።

በዚህም ደቡብ ምዕራብ፣ ሰሜን ምስራቅና ምስራቅ የአገሪቱን ክፍልና መካከለኛው የአገሪቱ ክፍል የበልግ ዝናብ ማግኘት የሚጀምሩ አካባቢዎች መሆኑን ነው የተገለጸው።

አብዛኛው የአገሪቱ አካባቢ ደግሞ አሁን ላይ ደረቃማ የአየር ሁኔታ እንደሚቀጥል ተጠቁሟል።

ይህም በውሃማ አካላት ላይ የትነት መጠን በመጨመር አሉታዊ ተጽእኖ እንዳለው ነው ኢንስቲትዩቱ በመግለጫው ያመላከተው።

ይህ ደረቃማ የአየር ሁኔታ የበልግ አብቃይ የሆኑ አካባቢዎች የግብርና ሥራ ላይም ተጽዕኖ እንደሚሳያርፍ ተገልጿል።

አልፎ አልፎ ባሉት ቀናት መጠነኛ የደመና ሽፋን በደቡብ፣ በደቡብ ምዕራብ፣ በስምጥ ሸለቆና አጎራባች በሆኑት አካባቢዎች ላይ መጠነኛ የደመና ሽፋን ሊኖር እንደሚችል ተመላክቷል።

ባለፉት አስር ቀናት አብዛኞቹ የአገሪቱ አካባቢ ደረቃማ ሁኔታ አመዝኖ እንደነበር ተገልጿል።

በእነዚህ ቀናት ሌሊትና ማለዳ ላይ ከ5 ዲግሪ ሴንትግሬድ በታችና አንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ከዜሮ ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በታች ማስመዝገባቸው በመግለጫው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም