የሰላም ስምምነቱ ለመልሶ ማቋቋምና መሰረተ ልማት ግንባታ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሰላም ስምምነቱ ለመልሶ ማቋቋምና መሰረተ ልማት ግንባታ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ነው
ድሬዳዋ (ኢዜአ) የካቲት 7/2015 የሰላም ስምምነቱ በጦርነትና በተፈጥሮ አደጋ የተጎዱ ዜጎችን ለማቋቋምና መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት አስታዋጾ እያደረገ መሆኑን የአማራ፣ አፋርና ሶማሌ ክልሎች የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነሮች ገለጹ።
የፌደራል እና የክልሎች የአደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽነሮች በኢትዮጵያ የአደጋ ስጋትን ለመቀነስና ለመከላከል ያከናወኗቸውን የስድስት ወር ስራዎች የገመገመ መድረክ በድሬዳዋ ተካሂዷል።
የአማራ፣ አፋርና ሶማሌ ክልሎች የአደጋ ስጋት አመራር ምክትል ኮሚሽኖች ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የተደረገው የሰላም ስምምነት በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ የተጎዱ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋምና ተገቢውን ሰብአዊ ድጋፍ ለማቅረብ የጎላ ሚና እየተጫወተ ነው።
የአማራ ክልል የአደጋ ስጋት አመራር ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ እታገኘው አደመ እንዳሉት፤ የሰላም ስምምነቱ በተለይ በጦርነት ቀጠናው ጉዳት የደረሰባቸውን መሠረተ ልማቶች መልሶ ለመገንባትና የተፈናቀሉ ወገኖችን ለማቋቋም እያስቻለ ነው።
ሰላም ለሁሉም መሠረት መሆኑን በአፅንኦት የገለጹት ኮሚሽነሯ፣ "በተለይ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎችን ቀድሞ ለመከላከልና በችግሩ ሳቢያ የተፈናቀሉትን ዜጎች ለማቋቋም ወሳኝ ነው" ብለዋል።
በፌደራል መንግስትና በህወሓት መካከል የሰላም ስምምነት መደረጉ በጦርነቱ ለተጎዱ የአማራ ክልል ተፈናቃዮች ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን የተሻለ ሰብአዊ ድጋፍ ለማቅረብና ለማቋቋም ማስቻሉን ገልፀዋል።
ተመሳሳይ ሃሶቦችን የገለጹት የአፋር ክልል የአደጋ ስጋት አመራር ምክትል ኮሚሽነር አሊ መሐመድ በበኩላቸው፣ "የሰላም ስምምነቱ ሰብዓዊ ድጋፍን በተሻለ ለማቅረብና ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም የተጀመሩ ተግባራት እንዲፋጠኑ እያገዘ ነው" ብለዋል።
የሰላም ስምምነቱ በክልሉ በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ የማቋቋምና የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ የመገንባት ሥራዎች ተገቢ ትኩረትና ድጋፍ እንዲያገኙ ማስቻሉንም ገልጸዋል።
መንግስት በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና በጦርነት ቀጠና የነበሩ አካባቢዎች ሰላም እንዲሆኑ ያሳየው ቁርጠኝነት ለሀገር ሰላም፣ ልማትና ዕድገት አበርክቶው የጎላ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሶማሌ ክልል የአደጋ ስጋት አመራር ምክትል ኮሚሽነር አብዱልፈታህ መሐመድ ናቸው።
እንደእሳቸው ገለጻ የተፈጠረው ሰላም በተለይ በሶማሌ ክልል በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች የተጎዱ ዜጎችን ለመደገፍና መልሶ ለማቋቋም አስተዋጾው የጎላ ነው።
በክልሉ በተለያዩ ምክንያቶች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በዘላቂነት የማቋቋምና ተፈጥሯዊ አደጋዎችን የመቀነስ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።
በድሬዳዋ ለሦስት ቀናት የተካሄደው የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽንና የክልሎች የስድስት ወራት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ግምገማ ማጠቃለያ ተከትሎ በድሬዳዋ እና በሶማሌ ክልል ሽንሌ ወረዳ የተከናወኑት የልማት ሥራዎች ተጎብኝተዋል።