ቀጥታ፡

የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚሰሩት ሥራዎች አበረታች ውጤት አስገኝተዋል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 7/2015 የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚሰሩት ሥራዎች አበረታች ውጤት ማስገኘታቸውን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ገለጸ።

በቡናና ሻይ ባለሥልጣን የቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍቃዱ አደፍርስ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል።

ይህንንም ተከትሎ የቡና ምርት ባልተለመደባቸው አካባቢዎችን የቡና ተክል ልማት የማስፋፋትና ስትራቴጂን በመከተል ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ነው ያስረዱት።

ጎን ለጎንም በበሽታ የተጠቁና በእርጅና ምክንያት ምርት የቀነሱ ቡናዎችን የመጎንደልና የነቅሎ ተከላ ሥራ በማከናወን ምርትና ምርታማነትን በማስፋት አመርቂ ውጤት መገኘቱን ጠቁመዋል።

ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በተካሄደው አገር አቀፍ የቡና ማደስ ሥራ 392 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተተከለ ቡና የመጎንደልና የነቅሎ ተከላ ሥራ መስራት መቻሉን ገልጸዋል።

አሁን ላይም በ135 ሺህ 911 ሄክታር መሬት ላይ የተተከለ ቡናን ለማደስ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ይህም የቡና ጥራት ለማሻሻል፤ የአርሶ አደሩን ገቢና አገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል።

ለአብነትም በዘንድሮ የምርት ዘመን ለማግኘት ከታቀደው 810 ሺህ ቶን ውስጥ 761 ሺህ ቶን የቡና ምርት ማግኘት ማቻሉን ገልጸው ይህም አምና ከተገኘው የ562 ሺህ ቶን ምርት ጋር ሲነጻጻር ከፍተኛ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።

ከምርታማነት አንጻር ባለፈው ዓመት አማካኝ ምርት በሄክታር 7 ኩንታል ሲሆን በዘንድሮው ዓመት ወደ 7 ነጥብ 17 ኩንታል በሄክታር ማሳደግ መቻሉንም ነው የገለጹት።

በተጨማሪም ምርታማነትን ለማሳደግ ወሳኝ የሆነውን ኮምፖስት ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ ሲሆን በምርት ዘመኑ 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ቶን በማዘጋጀት በ720 ሺህ ሄክታር ማሳ ላይ ለመጠቀም ተችሏል ብለዋል።

በቀጣይም ምርታማነትን በእጥፍ ለማሳደግ ያልታደሱ ቡናዎች ማደስና የእንክብካቤ ሥራዎችን ፓኬጁን ባሟላ መልኩ ለማከናወን በከፍተኛ ርብርብና ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

አሁን ያለው ምርታማነት ከሌሎች አገራት ጋር ሲነጻጸር እና ከማምረት አቅማችን ጋር ሲታይ ምርታማነታችንን በእጥፍ ለማሳደግ ብዙ ሥራዎች መሥራት ይገባል ነው ያሉት።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት የብራዚል፣ ኮሎቢያ፣ ቬትናምና የመሳሰሉ አገራት በሄክታር ከ12 እስከ 15 ኩንታል ቡና ማምረት ችለዋል።

በኢትዮጵያም ሞደል አርሶ አደሮች በሄክታር እስከ አስራ አምስት ኩንታል ቡና እያመረቱ መሆኑን ከባለሥልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም