ቀጥታ፡

የጉምሩክ ኮሚሽን በማሻሻያ ስራዎቹ ሕገ ወጥነትን የመከላከል አቅሙን እያጎለበተ መሆኑን ገለጸ

ሐዋሳ (ኢዜአ) የካቲት 7/2015 የጉምሩክ ኮሚሽን በማሻሻያ ስራዎቹ ሕገ ወጥነትን የመከላከል አቅሙን እያሳደገ መሆኑን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲና ከደቡብ ፖሊስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር ከየክልሉ ለቅጥር የመለመላቸውን ጀማሪ የጉምሩክ ኦፊሰሮች በይርጋለም ከተማ ለሶስት ወራት የሚሰጠውን ስልጠና ዛሬ አስጀምሯል።

የጉምሩክ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሙሉጌታ በየነ እንዳሉት፤ ኮሚሽኑ ራሱን ችሎ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ የሕግ ተገዢነት፣ አሰራር፣ የመዋቅርና የአደረጃጀትና ተቋማዊ አቅም ግንባታን ጨምሮ የተለያዩ ማሻሻያዎች እያደረገ ነው።

ማሻሻያዎቹ ሎጀስቲክስን በማሳለጥና በገቢ አሰባሰብ ረገድ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።

የኮሚሽኑ የገቢ አሰባሰብ በየዓመቱ ከ30 በመቶ በላይ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉንና "ከሀገራዊ ገቢ እስከ 45 በመቶ ይሸፍናል" ሲሉ ገልጸዋል።

ኮንትሮባንድንና የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል በተደረገው ጥረት ማህበረሰቡንና ኢኮኖሚውን ሊጎዱ የሚችሉ እና በደህንነት ላይ የተጠቃጡ አደጋዎችን መመከት እንደተቻለም ነው ምክትል ኮሚሽነሩ ያስረዱት።

ዓለም የደረሰበትን የኦንላይን የደንበኞች አገልግሎት በመስጠት የተሻለ ስራ ቢከናወንም ነገር ግን ከፊት ብዙ ስራዎች እንዳሉ ጠቁመዋል።

በተለይም ኮንትሮባንድ፣ ንግድ ማጭበርበርና ሕገ-ወጥ ንግድ አሁንም በሚፈለገው ልክ ያልተፈቱ ችግሮች ናቸው ብለዋል።

ኮሚሽኑ እነዚህን ፈተናዎች ለመቀልበስ ስትራቴጂ ቀይሶ እየሰራ መሆኑን አክለዋል።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን አበበ በበኩላቸው የጉምሩክ ኦፊሰሮች ሀገራቸውን የሚወዱ፣ ለሙያቸው ታማኝና ታታሪ ሊሆኑ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከሚሰጠው ፖሊሳዊ ሳይንስ ስልጠና በተጓዳኝ ለጉምሩክ ኮሚሽን ባለሙያዎች በቀጥታ ከስራው ጋር የተያያዘ ስልጠና በቅንጅት እንደሚሰጥም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም