በቡና ምርትና ገቢ ላይ የታየው መነቃቃት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው -ዶክተር ግርማ አመንቴ - ኢዜአ አማርኛ
በቡና ምርትና ገቢ ላይ የታየው መነቃቃት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው -ዶክተር ግርማ አመንቴ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 7/2015 በቡና ምርትና ገቢ ላይ የታየው መነቃቃት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ አስታወቁ።
የኢትዮጵያ ቡና ማኅበር 50ኛ ዓመት የወርቅ እዩቤልዩ የምሥረታ በዓል ተከብሯል።
በበዓሉ አከባበር ላይ የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ፣ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፣ አምራቾችና ላኪዎች ተሳትፈዋል።
ዶክተር ግርማ አመንቴ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት መንግሥት ዘርፉን ለማነቃቃት አርሶ አደሩ ድጋፍ የሚያገኝበት አሰራሮችና መመሪያዎች እየተገበረ ነው።
በተለይም የልዩ ጣዕም ቡና ውድድር መጀመሩ የአርሶ አደሩ ገቢ እንዲጨምር ማድረጉን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ የቡና ምርታማነት እንዲያድግ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ ቡናን በኩታ ገጠም ማምረትና ጉንደላዎችን/እደሳ/ን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራዊ እየተሰሩ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ቡና ማኅበር የቦርድ ፕሬዝዳንት ደሳለኝ ጀና እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ ዋነኛ የውጭ ገቢ ምንጭ የሆነው ቡና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን ማኅበሩ የድርሻውን ሲወጣ ቆይቷል።
አገሪቱ ከቡና የምታገኘው ገቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ለዚህም የማህበሩ ሚና ከፍ ያለ መሆኑን አስታውሰዋል።
ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ ከቡና የወጪ ንግድ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷ ትልቅ ውጤት ቢሆንም ካለው እምቅ ኃብት አኳያ የበለጠ መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
ማኅበሩ አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን በማስፋት ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ ከፍ እንዲል እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም ማኅበሩ ጥቂት የገበያ መዳረሻዎች ብቻ እንደነበሩት የጠቆሙት ፕሬዝዳንቱ፤ በአሁኑ ወቅት ከ60 በላይ አገራት የቡና ምርት እየላከ መሆኑን ተናግረዋል።
ማኅበሩ አገሪቱ ከቡና የምታገኘውን ጥቅም የበለጠ ለማሳደግ ግብ መንደፉን ያስረዱት አቶ ደሳለኝ፤ ዘመናዊ የቡና ቤተ-ሙከራ፣ የገበያ ምርምር ተቋም፣ የቡና ግብይት ሥልጠና ማዕከል ግንባታ ከዕቅዶቹ መካከል ተጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ በበኩላቸው፤በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን ቡና ላይ እሴት የመጨመሩ ጉዳይ አጽንኦት ሊሰጠው እንደሚገባ አመልክተዋል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ጉዳይ አስፈጻሚ አምባሳደር ትሬሲ አን ጃኮብሰን፤ ኢትዮጵያ የቡና መገኛም ብቻ ሳትሆን የተለየ ጣዕም ያለው ቡና ባለቤት ናት ብለዋል።
የአሜሪካ መንግሥት ዘርፉን ለመደገፍ 50 ሚሊዮን ዶላር ፈሰስ ማድረጉን የገለጹት አምባሳደር ትሬሲ አን ጃኮብሰን ፤ በአሜሪካ ተራድኦ ድርጅትና በአሜሪካ ግብርና ተቋም በኩል ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ የቡናው ዘርፍ እንዲነቃቃ እና የግሉ ዘርፍ እንዲጠናከር የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ያረጋገጡት።
የኢትዮጵያ ቡና ማኅበር ሲቋቋም ጥቂት አባላት ብቻ የነበሩት ሲሆን በአሁኑ ወቅት በኀብረት ሥራ ማኅበራት የታቀፉ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን አርሶ አደሮች፣ ጥሬ እና የተቆላ ቡና ላኪዎችን በአባልነት ያቀፈ ነው።