የጅቡቲ ባለሀብቶች በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ገብተው እንዲሰሩ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል-የጅቡቲ የንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የሱፍ ሙሳ ዳዋሌህ - ኢዜአ አማርኛ
የጅቡቲ ባለሀብቶች በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ገብተው እንዲሰሩ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል-የጅቡቲ የንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የሱፍ ሙሳ ዳዋሌህ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 7/2015 የጅቡቲ ባለሀብቶች በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ገብተው እንዲሰሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ የጅቡቲ የንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የሱፍ ሙሳ ዳዋሌህ ገለጹ።
በጅቡቲ የንግድ ምክር-ቤት ፕሬዚዳንት የሱፍ ሙሳ ዳዋሌህ የተመራ ልዑክ የቂሊንጦ እና ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ጎብኝቷል።
የጅቡቲ የንግድ ምክር ቤት ልዑካን ቡድን አባላቱ የኢትዮጵያ እና የጅቡቲን የንግድና የኢንቨስትመንት ትስስር ይበልጥ ለማጠናከርና ለማስተዋወቅ ያለመ ጉብኝት በኢትዮጵያ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
የልዑካን ቡድኑን የተቀበሉት በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ሰለሞን ናቸው።
በጉብኝታቸውም በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ የተከናወኑ የልማት ስራዎችንና የባለሀብቶችን እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱም በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች፤ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በኢንቨስትመንት አማራጮች፣ ለባለሀብቶች ስለሚደረጉ ማበረታቻዎች እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ በተሰሩ ስራዎች ዙሪያ ገለፃ ተደርጎላቸዋል።
የጅቡቲ የንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የሱፍ ሙሳ ዳዋሌህ በጉብኝቱ ወቅት በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ያለው የኢንቨስትመንት አማራጭ በጅቡቲ የሚገኙ ባለሃብቶች በፓርኮቹ ገብተው ኢንዲሰሩ የሚያበረታታ ነው ብለዋል።
የጅቡቲ ባለሀብቶች በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ገብተው እንዲሰሩ አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግ የጅቡቲ የንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ሰለሞን በበኩላቸው የልዑካን ቡድኑ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን መጎብኘታቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድና የኢንቨስትመንት ትስስር ያጠናክራል ብለዋል።
ጉብኝቱ ከጅቡቲ በቅርብ ርቀት ላይ በተገነባው የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ውስጥ የጅቡቲ ባለሀብቶች ገብተው መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ የሚያነቃቃ ነው ማለታቸውን ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡