በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው መቀጠል አለባቸው - ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ቡድን - ኢዜአ አማርኛ
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው መቀጠል አለባቸው - ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ቡድን
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 07/2015 በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ዓለም አቀፉ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ቡድን ገለጸ።
የተግባር ቡድኑ 8 ነጥብ 2 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚገመት የሕክምና መገልገያ ቁሳቁስ ወደ አገር ቤት እንዲገባ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።
ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ቡድን የቦርድ ዳይሬክተር አለማየሁ አበበ እና የቦርዱ ዋና ጸሐፊ አምሳለ ገሰሰ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ጉዳይ ላይ ስለሚኖራቸው ተሳትፎ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በቆይታቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የ1 ሚሊዮን ዳያስፖራ አገር ቤት ጥሪን ተከትሎ ማህበሩ ንቁ ተሳትፎ ማድረጉን አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያ ጦርነት ላይ በነበረችበት ወቅት የተለያዩ የሕክምና መገልገያ ቁሳቁሶችን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርጉ መቆየታቸውን አንስተዋል።
የተግባር ቡድኑ የቦርድ ዳይሬክተር አለማየሁ አበበ እንዳሉት፤ ማህበሩ በተቋቋመ በአጭር ጊዜ ውስጥ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር ሰፊ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
በቅርቡ 8 ነጥብ 2 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚገመት የሕክምና መገልገያ ቁሳቁስ ወደ አገር ቤት እንዲገባ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
የተግባር ቡድኑ የቦርድ ዋና ጸሃፊ አምሳል ገሰሰ በበኩላቸው፤ በጦርነት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ሴቶች የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች ለተጠለሉ ዜጎች የሚውል የ100 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ገቢ በማሰባሰብ ድጋፍ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።
ባለፈው የፈረንጆቹ 2022 በውጭ የሚኖሩ ናይጄሪያውያን 17 ነጥብ 6 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለአገራቸው በመላክ ከአፍሪካ ግንባር ቀደም መሆናቸውን ተናግረዋል።
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከናይጄሪያውያን ትምህርት በመውሰድ ለአገራቸው የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ማህበሩ በቀጣይ በትምህርት ቤቶች እና ሌሎች መሰረተ-ልማት ግንባታ ላይ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ቡድኑ እያደረገ የሚገኘው የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ ከኢትዮጵያውያን በሚያገኘው ገንዘብ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይም የሚደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቋል።
መንግሥት ለአገራቸው አስተዋጽኦ ላበረከቱ የዳያስፖራ አደረጃጀቶችና አባላት የሰጠው እውቅና ለበለጠ ሥራ እንደሚያነሳሳ ጠቁመዋል።
የተግባር ቡድኑ በተለያዩ የሙያ ዘርፍ ብቁ የሆኑ ኢትዮጵያውያን በሚችሉት የሙያ መስክ ለአገራቸው ድጋፍ እንዲያደርጉ እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
በቀጣይም ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው የሚያደርጉትን ድጋፍ እና ኢንቨስትመንት አጠናክረው እንዲያስቀጥሉም መንግሥት አሰራሮችን ምቹ ማድረግ እንደሚኖርበት ተናግረዋል።
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ብሔራዊ ጥቅም መጠበቅ እያደረጉ ያለውን አኩሪ ትግል አጠናክረው በመቀጠል በሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው ጠይቀዋል።
ግሎባል የኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ አክሽን ግሩፕ(ግ.ኢ.ዳ.አ.ግ) 2014 ዓ.ም በውጭ በሚኖሩ ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን የተቋቋመ የሲቪክ ድርጅት ነው።