ቀጥታ፡

በ44ኛው የዓለም የአገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ዛሬ ሌሊት ወደ ስፍራው ያቀናል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 6/2015 በ44ኛው የዓለም የአገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ የሚሳተፈው ልዑካን ቡድን ዛሬ ሌሊት ወደ አውስትራሊያ እንደሚያቀና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታወቀ44ኛው የዓለም የአገር አቋራጭ ሻምፒዮና የካቲት 11 ቀን 2015 ዓ.ም በአውስትራሊያ ባትረስ ከተማ ይካሄዳል።

ኢትዮጵያም በዚህ ሻምፒዮና የምትካፈል ሲሆን ተሳታፊ አትሌቶች ከጥር 3 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ልምምዳቸው ሲሰሩ ቆይተዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ዮሐንስ እንግዳ ለኢዜአ እንደገለጹት በዚህ ሻምፒዮና የሚሳተፉ አትሌቶችና ሌሎች የልዑካን ቡድን አባላት ዛሬ ሌሊት 7፡00 ሰዓት ላይ ወደ ስፍራው ያቀናሉ።

ፌዴሬሽኑ በዚህ አገር አቋራጭ ሻምፒዮና 28 ዋና ተሳታፊ አትሌቶችና ሌሎች ተጠባባቂ አትሌቶችን ይዞ ከፍተኛ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ጠቁመዋል።

የካቲት 11 ቀን 2015 ዓ.ም በሚካሄደው 44ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ በአዋቂ ወንዶችና ሴቶች 10 ኪሎ ሜትር ውድድር፣ በወጣት ወንዶች 8 ኪሎ ሜትር፣ በወጣት ሴቶች 6 ኪሎ ሜትር እና በ8 ኪሎ ሜትር ድብልቅ ዱላ ቅብብል(ሪሌ) የምትካፈል ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም