ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሀኪሞች ማህበር የእናቶችና ጨቅላ ሕፃናት ሞትን ለመቀነስ የሚያደርገውን ድጋፍ ይበልጥ እንዲያጠናክር ተጠየቀ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 6/2015 የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሀኪሞች ማህበር የእናቶችና ጨቅላ ሕፃናትን ሞት ለመቀነስ እያደረገ ያለውን ያልተቋረጠ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል የጤና ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ።

ማህበሩ ለሁለት ቀናት የሚያካሄደው 31ኛ ዓመታዊ ጉባዔ ዛሬ ተጀምሯል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ማህበሩ ከጤና ሚኒስቴር ፕሮጀክቶችን ተረክቦ ተግባራዊ በማድረግ የጤና ችግሮች እንዲፈቱ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው ብለዋል።

የእናቶች ሞት ምክንያት የሆኑትን የደም መፍሰስና ከውርጃ ጋር ተያይዞ ያሉ የጤና ችግሮችን በመፍታት ረገድ ያለውን አበርክቶ በዋንኛ ማሳያነት አቅርበዋል።

ማህበሩ በጽንስና ማህጸን ሕክምና ዘርፍ የጥናትና ምርምር ስራዎች በመሳተፍ እንዲሁም የጤና ባለሙያዎችን እያሰለጠነ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በእናቶችና ጨቅላ ሕፃናትን ሞት መቀነስ ፕሮጀክቶች ላይ የሚያደርገውን ያልተቋረጠ ድጋፍ ማህበሩ አጠናክሮ እንዲቀጥል ነው ዶክተር አየለ ጥሪ ያቀረቡት።

የኢትዮጵያ ጽንስና ማህጸን ሀኪሞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር አብዱልፈታህ አብዱልቃድር በበኩላቸው ማህበሩ ላለፉት 31 ዓመታት በእናቶችና ጨቅላ ሕፃናት ጤና መሻሻል የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችንና ለባለሙያዎች ስልጠናዎችን እየሰጠ መሆኑን አመልክተዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች በግጭት የተጎዱ የጤና ተቋማትን መልሶ በማቋቋም ስራ ላይም የነቃ ተሳትፎ አድርጓል ነው ያሉት ዶክተር አብዱልፈታህ።

ማህበሩ በጤናው ዘርፍ ለፖሊሲ ግብአት የሚሆኑ ምክረ ሃሳቦችን እያቀረበ እንደሚገኝም በመጠቆም።

የእናቶችና ጨቅላ ሕፃናት ጤና እንዲሻሻል ከጤና ሚኒስቴርና ከጤና አጋሮች ጋር በትብብር እየሰራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሀኪሞች ማህበር በዓመታዊ ጉባኤ መክፈቻው ላይ በጤናው ዘርፍ በእናቶችና በጨቅላ ሕጻናት ጤና መሻሻልና በጤና ፖሊሲ ላይ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና እና ሽልማት ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም