የመንግስታቱ ድርጅት በአፍሪካ ለወቅታዊ የሚቲዎሮሎጂ መረጃ ተደራሽነት የሚያግዝ 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ሊያደርግ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመንግስታቱ ድርጅት በአፍሪካ ለወቅታዊ የሚቲዎሮሎጂ መረጃ ተደራሽነት የሚያግዝ 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ሊያደርግ ነው
አዲስ አበባ (ኢዜአ)የካቲት 6/2015 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአፍሪካ ወቅታዊና ተዓማኒ የሚቲዎሮሎጂ መረጃ ለተጠቃሚው ማህበረሰብ ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል የ3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርግ የዓለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት ረዳት ሴክሬታሪ ጀኔራል ዶክተር ዌንጂያ ዥንግ ገለጹ፡፡
በዓለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት "የአፍሪካ ቀጣናዊ ትብብር ማህበር-1" 54 አባል ሀገራት የሚሳተፉበትን 18ኛው ስብሰባ በአዲስ አበባ ከተማ እያካሔደ ነው፡፡
ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት በሚቆየው የአፍሪካ ቀጣናዊ ትብብር-1 አባል ሀገራት ስብሰባ የሚቲዎሮሎጂና ሀይድሮሎጂ ዳይሬክተሮች እንዲሁም አጋር አካላት እየተሳተፉ ነው፡፡
የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት ረዳት ሴክሬታሪ ጀኔራል ዶክተር ዌንጂያ ዥንግ፤ አፍሪካ በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት ከፍተኛ ችግር እያጋጠማት ነው፡፡
እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ2022 በናይጀሪያ ብቻ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሰዎች በጎርፍ አደጋ የከፋ ጉዳት ማስተናገዳቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በምስራቅ አፍሪካ በኢትዮጲያ፣ ኬንያ፣ ሱዳን እና ሶማሊያ ከ13 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለምግብ እጥረት ተዳርገዋል ብለዋል፡፡
እየጨመረ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተፅዕኖ በዘላቂነት ለመፍታት የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት ከአፍሪካ (RA-1) አባል አገራት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት አሰራሩን በማዘመን ወቅታዊና ተዓማኒ የሚቲዎሮሎጂ መረጃ ለማዳረስ ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚውል የ3 ነጥብ 1 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ፤ የአፍሪካ ቀጣናዊ ትብብር ማህበር -1 ስብሰባ በአፍሪካ ያለውን የሚቲዎሮሎጂ ምልከታ ማጠናከር ያስችላል ብለዋል፡፡
የሚቲዎሮሎጂ ትንበያ፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያና የቴክኖሎጂ ምርምር ዘርፎችን ያካተቱ ምክረ ሃሳቦች የሚቀርቡበት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ወቅታዊና ታዓማኒነት ያለው የሚቲዎሮሎጂ መረጃ ለተጠቃሚው ማህበረሰብ ተደራሽ ለማድረግ በቴክኖሎጂ የዳበረ አሰራር መከተል ለነገ የሚባል አይደለም ብለዋል፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አብርሃ አዱኛ፤ የአፍሪካ ቀጠናዊ ትብብር ማህበር -1 ስብሰባ አፍሪካውያን የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋምይበልጥ እንዲተባበሩ ያደርጋል ብለዋል፡፡