የሳይንስ ሙዚየም የአዲስ ምዕራፍ መክፈቻ !

ሳይንስ ዕውቀትነቱ በዘመናት ሂደት ውስጥ በቃል ከመነገር በጽሑፍ ከመስፈር አልፎ የሚዳሰስ የሚታይ የተግባር መገለጫ ወደ መሆን መሻገሩን ባለንበት ዘመን የሳይንስ ውጤት የሆኑ የፈጠራ ስራዎችን በአብነት መጥቀስ ይቻላል።

የሳይንስ ተግባር የሰውን ልጅ ሕይወት ለማሻሻል ፈጠራዎችን ማበርከት፣ ክስተቶችን በተጨባጭ አመክኖይ መተንተን፣ ማስረዳት እና መተንበይ ሲሆን፤ ከሳይንስ ቱሩፋቶች መካከል የዘርፉ ጽንሰ ሀሳቦችና ፈጠራዎች ስብስብ ውጤት የሆነው ቴክኖሎጂ ይጠቀሳል።

ከስፔስ ሳይንስ ጀምሮ፣ በዕለት ተዕለት እስከ ምንጠቀምባቸው ትራንስፖርት፣ ልብስ፣ ምግብ፣ መድኃኒት፣ ስፖርት ድረስ የዘለቀው የቴክኖሎጂ ፈጠራ የሰውን ልጅ የሕይወት ውጣ ውረድ በማቅለል የሳይንስን አሻራ ሕይወታችን ጋር አዛምዶታል።

የቴክኖሎጂ ውጤቶች መፈተሻና መነሻ ሆነው ከሚያገልግሉ ተቋማት መካከል ግንባር ቀደሙን የሚይዙት የሳይንስ ምርምር ተቋማት ናቸው። ኢትዮጵያም በዩኒቨርስቲዎቹ ከመሰረተቻቸው የምርምር ተቋማት ባለፈ ከዘርፉ በላቀ ሁኔታ እንድትጠቀምና ልጆቿን ለማብቃት የሚያስችላትን የሳይንስ ሙዚየም ገንብታለች።

ሙዚየሙ ሳይንስና ጥበብን አጣምሮ በያዘ የኪነ-ህንጻ ንድፍ የተገነባ ነው። ኪነ ህንጻው የያዘው ክብ ቅርፅም በማያቋርጥ ሂደት ውስጥ ያለ እድገትና የሰው ልጆችን ጥበብ የሚያመለክትና በተጓዳኝም ኢትዮጵያ በአስገራሚ ፍጥነት በማደግ ላይ ካለው ቴክኖሎጂ ጋር ለመጣመር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።

የሳይንስ ሙዚየሙን በተመረቀበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንደገለጹት፤   የሳይንስ ሙዚየም በሌሎች አገሮች ተገንብቶና በተግባር ህዝቦቻቸው ሲገለገሉ በተመለከቱ ወቅት ሁሉ በኢትዮጵያ እውን ባለመሆኑ ተቆጭተዋል፤ ተገንበቶ ለማየት ጓጉተዋል። ለዚህም ነው ለኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ህልም እንደነበር ያነሱት። 

የሳይንስ ሙዚየሙን የወደፊት ትሩፋት ሲያመለክቱም፤ “የተሻለች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በልጆች ላይ መሰረት የሚጥል ነው።ህልም የነበረው ጉዳይ እውን ሆኖ ሁለገብና አስደናቂ የሳይንስ ሙዚየም በአዲስ አበባ ተገንብቷል” ብለዋል።

የሳይንስ ሙዚየም ህጻናትና ወጣቶች የፈጠራ ሀሳቦችን እንዲለማመዱና እንዲያሳድጉ የሚያስችሉ ማዕከላት እንዳሉትና የተሻለች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ለሚደረገው ጥረት መሰረት የሚጥል መሆኑም ተመልክቷል።

ኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገ ካለው ቴክኖሎጂ ጋር አብሮ ለመሄድ ያላትን ቁርጠኝነት በሚያሳየው የሳይንስ ሙዚየም የተለያዩ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ውጤቶች ለእይታ የቀረቡ ሲሆን፤ የቀደመውንየአሁኑንና የወደፊት ሁኔታን በሳይንሳዊ ጥበብ በማጣመር ለተመራማሪዎች፣ ለተማሪዎች፣ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ መነሻ የሚሆኑ ጉዳዮች ተካተዋል።

በሳይንስ ሙዚየሙ ከግብርና እስከ ደኅንነት የሚደርሱ  ማህበረ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን የሚፈትሹ ፈጠራዎች ቀርበዋል።እነዚህም አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ ጋላክሲ፣ ሮቦቲክስን ጨምሮ ለሳይንስ የጠለቀ ግንዛቤ ለመያዝ የሚያስችሉ ግኝቶች ናቸው።

የሳይንስ ሙዚየሙ ከተመረቀ በኋላ የአገሮች መሪዎች፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎችን ጨምሮ ከአንድ ሚሊዮን  በላይ የሚሆኑ ሰዎች ጎብኝተውታል።

ከጎብኚዎቹ መካከል ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡ አፍሪካውያን መሀንዲሶች እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ የተገነባው የሳይንስ ሙዚየም አፍሪካን በሳይንስ ዘርፍ ወደ ፊት ለማሻገር አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው።

ኢትዮጵያ በዘርፉ እያከናነወች ያለው ስራ በሌሎች የአፍሪካ አገሮችም ሊተገበር የሚገባው መሆኑን ይናገራሉ።

በሳይንስ ሙዚየሙ ጉብኝት ከተደነቁ የአፍሪካ ልጆች መካከልም ጋዜጠኞች ይገኙበታል። ከጋና፣ ካሜሮን፣ ኒጀር፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሩዋንዳና ሌሎች አገሮች የተውጣጣና የአፍሪካን ገፅታ ለመገንባት የተቋቋመው የአፍሪካ ህብረት የመገናኛ ብዙሃን ቡድን የኢትዮጵያ ሳይንስ ሙዚየምን ጎብኝቷል።

ጎብኚዎቹ እንደገለጹት፤ በሙዚየሙ ውስጥ ለኢትዮጵያ እንዲሁም ለአፍሪካ እድገት አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉ የሳይንስና ፈጠራ ስራዎችን መመልከታቸውን ነው ያመለከቱት።

የሳይንስ ሙዚየሙ አፍሪካን የግጭት፣ የድህነትና የኋላቀርነት አህጉር እንደሆነች ተደርጎ የሚቀርበውን የተሳሳተ ትርክት በመቀየር አህጉሪቷ የተስፋ ጎህ እየፈነጠቀባት የምትገኝ ስለመሆኗ ምስክር መሆኑንንም ነው ያመላከቱት።

የአፍሪካ ህብረት የኮሙዩኒኬሽን ሃላፊ ውይኒ ሙሳባያና በበኩላቸው ሙዚየሙ ለአፍሪካውያን ዓይን ገላጭ ነው” ብለዋል።

ዓለም በአፍሪካ ላይ ያለውን የተሳሳተ ትርክት ለማስተካከልና የአፍሪካ ህብረት ለሚሰራው የተግባቦት ስራም የኢትዮጵያ ሳይንስ ሙዚየም አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑንም አክለዋል።

በቴክኖሎጂና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የቀረቡ የፈጠራ ውጤቶች አፍሪካ ለችግሮቿ መፍትሄ ማምጣት የምትችል አህጉር መሆኗን ያሳያል።

በብሔራዊ ሳይንስ ሙዚየም አጠቃላይ ተልዕኮና እንቅስቃሴ ዙርያ ከኢዜአ  ጋር ቆይታ  ያደረጉት  የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ተስፋዬ ዘውዴ፤ “ብሔራዊ የሳይንስ ሙዚየም ለወጣቶች በዘርፉ እንዲሰማሩ ከሚፈጥረው መነሳሳት ባለፈ ባለሙያዎች የምርምር ስራዎቻቸውን ለማቅረብ የሚያስችል ቦታ ሆኗል” ይላሉ።

ይህም የፖሊስ አውጪዎች፣ የቢዝነስ አጋሮችና የተቋማት ኃላፊዎች ከባለሙያዎች ጋር ትስስር እንዲፈጥሩ የሚያስችል ሲሆን፤ በአገራችን ለሳይንስ የተሰጠውን ትኩረት ተከትሎም ታዳጊዎችና ወጣቶች በሙዚየሙ በሚያዩት የፈጠራ ውጤቶቸ መነሻ ሀሳብ ይሆናቸዋል።

“የሳይንስ ሙዚየሙ አፍሪካ ለሳይንስ ፈጠራ የሚታትሩ ልጆችና እጆች እንዳሏት ምልክት የሚሆንና መዳረሻ ጉዞዋንም የሚያሳይ ገጽ ነው” የሚሉት አቶ ተስፋዬ፤ በሙዚየሙ የቀረቡትም የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሰራሽ ልህቀት፣ ክህሎት) እና የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ለዚህ ማሳያ መሆናቸውን ነው ያስረዱት።

በሙዚየሙ ለእያታ ከቀረቡት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስና የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች መካከል የጤና  ሮቦቲክ፣ የትምህርት፣ ፋይናንስ፣ ግብርና ፣ ትራንስፖርትና ደኅንነት ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ ፈጠራዎች አፍሪካዊ የአኗኗር ፀባይና ማህበራዊ ሁኔታን ባገናዘበ መልኩ የተሰሩ መሆናቸውን አንስተዋል።

ይህ የሳይንስ ሙዚየም በቴክኖሎጂ የሚፈቱ ችግሮችን በመለየትና በተለይም በግብርና፣ በጤና፣ በትራንስፖርት፣ ቱሪዝምና ትምህርት ዘርፍ መሠረታዊ ለውጦችን ለማስመዝገም ሚናው የጎላ ይሆናል።

ሳይንስና ጥበብን በጋራ አጣምሮ በያዘ የኪነ-ህንጻ ንድፍ የተገነባውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሳይንስ ሙዚየም በ6 ነጥብ 78 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፤ ሙዚየሙ ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ የሳይንስ እድገት ከፍተኛ አበርክቶ ይኖረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም