ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ - የአፍሪካ የዘመናት ፈተና

በረከት ሲሳይ

በርካታ የአፍሪካ አገራት ነፃነታቸውን ከተቀዳጁበት ከ1960ዎቹ ጀምሮ እስካሁን እልባት ካልተገኘላቸው አፍሪካዊ ጉዳዮች መካከል ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ አንዱ ነው። ለዚሁ ጉዳይ በርካታ መነሾ ቢኖሩትም ቅኝ ግዛቱ የፈጠራቸው ፖለቲካዊ ስንጥቃቶች፣ ድህነትና ሌሎች ማኅበራዊ ምስቅልቅሎሽ ለእነዚህ የጸጥታ ችግሮች በአብዛኛው የሚነሱ ምክንያቶች ናቸው። በአህጉሪቱ ላለፉት 40 እና 50 ዓመታት መቋጫ በሌለው መልኩ እዚህም እዚያም የሚነሱ ግጭቶችና ጦርነቶች ለአያሌዎች ሞትና የአካል ጉዳተኝነት ለገሚሱ ደግሞ ለዘመናት ከኖረበት ቀዬ እንዲሰደድ ምክንያት ሆነዋል።

በብዙ ጥረት የተገነቡ መሰረተ-ልማቶች ወደ ፍርስራሽነት እንዲለወጡና በሂደት ላይ ያሉ የዘመናዊ አገር ግንባታ ሂደቶች እንዲስተጓጎሉና በፈተናዎች እንዲታጀቡ አድርጓል። ይህንኑ ኢኮኖሚያዊ ኪሣራ በሚያሳይ መልኩ፤ የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ከሁለት ዓመታት በፊት ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው፤ በአፍሪካ የሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮች በየዓመቱ የአገራቱን አጠቃላይ አገራዊ ምርት (ጂ ዲ ፒ) እድገት ከ4 በመቶ እስከ 6 በመቶ እንዲቀንስ ያደርገዋል ይላል።

በተለይም ደግሞ በኢኮኖሚው ላይ የሚከሰቱ ችግሮች ተጽዕኖ ዓመታትን የሚዘልቅ በመሆኑ ተደራራቢና ድግግሞሽ ያሏቸው ችግሮች እንዲበራከቱ በር ከፍቷል። በእነዚህ ድርብርብ ውጥንቅጦች በአህጉሪቱ በከባድ ድህነት የሚኖሩ ዜጎች ህይወት ይበልጡኑ እንዲወሳሰብባቸውና ለከፋ ማኅበራዊ ችግር እንዲጋለጡ እያደረገ ነው። ከዚህም ባለፈ የጸጥታ ችግሮች በአፍሪካ ሳያባሩ መቀጠላቸው ዛሬም ጉዳዩን በአንክሮ እንድንመለከተው ያስገድደናል። ይህንን በሚያስረግጥ መልኩ ያለፈው የፈረንጆች ዓመት (2022) ግጭቶች የተስተዋሉበት ዓመትና በዘንድሮ ዓመት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ ተመላክቷል።

በሰላም ስምምነት የተቋጨውን በኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረውን ጦርነት ጨምሮ እስካሁን እልባት ያልተገኘላቸው የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና የደቡብ ሱዳን የጸጥታ ችግሮች ተጠቃሽ መሆናቸውን ነው የአፍሪካ የደኅንነት ተቋም ሪፖርት የሚያሳየው። ከዚህ ጎን ለጎን በሳሀል፣ በቻድ ሃይቅ ሸለቆ፣ በምስራቅ አፍሪካና በሰሜን ሞዛምቢክ ጸጥታን የሚያውክ የጽንፈኝነት እንቅስቃሴ መኖሩንም አመላክቷል።

ከዚህ ጎን ለጎን በቡርኪና ፋሶ፣ በጊኒ፣ ማሊ፣ ሱዳን፣ ቻድ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ጅቡቲ፣ ጊኒ ቢሳው፣ ማዳጋስካርና ኒጀር የተሳካና ያልተሳካ የመፈንቅለ-መንግሥት (ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ) ሙከራ መካሄዱንና የፖለቲካ አለመረጋጋት እንደተስተዋለባቸው ነው ሪፖርቱ ያወሳው። መንግሥታዊ የአስተዳደር ግድፈቶች፣ ምርጫን ተከትሎ የሚቀሰቀስ አለመግባባትና ሌሎችም በአህጉሪቱ ላለፉት ሁለት ዓመታት የተከሰቱ የጸጥታና የደኅንነት ችግሮች ለተያዘው የፈረንጆች ዓመትም ትልቅ ሥጋት መሆኑን ነው ያነሳው።

አፍሪካ ኅብረት በበርካታ አገሮች የጸጥታ ችግሮች እንዲቆሙና እንዲረጋጉ በማድረግ አዎንታዊ ሚና መጫወቱ ተገልጿል። ለአብነትም በኢትዮጵያ በዘላቂነት ግጭትን ለማቆም የተደረሰው የሰላም ስምምነት ተጠቃሽ ሲሆን በሌሎችም አገራት ወደ ተሻለ ፖለቲካዊ መረጋጋት እንዲመጡ ትልቅ ሥራ ሰርቷል።

ይህም ሆኖ አሁንም ድረስ ዘላቂ ሰላም በማረጋገጥ በኩል በርካታ ሥራ እንደሚቀር ነው የተገለጸው። በተለይም ደግሞ በምዕራብ ሳሀል ያለው ከአልቃይዳና ከአይ ኤስ ጋር ግንኙነት ያለው ጽንፈኛ ቡድን በአካባቢው የፈጠረው አለመረጋጋት፣ ከማሊ የፈረንሳይ ጦር መውጣትና ማሊ ራሷ ከሳሀል ቡድን አምስት የጸጥታ መዋቅር መውጣቷም ሌላው የአህጉሪቷና የአካባቢው ራስ ምታት ሆኗል።

የቻድ ሃይቅ ሸለቆ አካባቢ (በኒጀር፣ ቻድ፣ በካሜሮንና ናይጄሪያ) የሚስተዋለው የቦኮሃራምና ሌሎች የጽንፈኝነት እንቅስቃሴ፣ በምስራቃዊ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ራሱን ኤም23 በማለት የሚጠራው ቡድን ከማዕከላዊ መንግሥት ጋር ጦር መማዘዙ እንዲሁም በሰሜን ሞዛምቢክ ያለው በመንግሥትና በተቃዋሚ መካከል የተቀሰቀሰው የሽምቅ ውጊያ አሁንም አለመቆሙ፤ የአፍሪካ ኅብረት ጸጥታን በተመለከተ በዚህ ዓመት ትኩረት ሊያደርግበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ነው የእንግሊዙ ቻም ሃውስ የተሰኘው የጥናት ተቋም መረጃ የሚያመለክተው።

በተያዘው የፈረንጆች ዓመት በተለያዩ ደረጃ የሚካሄዱ 17 ብሔራዊ ምርጫ መኖራቸውንና ይህንንም ተከትሎ ሊከሰቱ የሚችሉ የድኅረ-ምርጫ ፖለቲካዊ ግጭቶችን በማስቀረት ረገድ አፍሪካ ኅብረት አዎንታዊ ሚና መጫወት እንደሚጠበቅበትም ተመላክቷል።

የአፍሪካ ኅብረት ቀጣይ አቅጣጫስ?

አፍሪካ ኅብረት በበርካቶች አይን ሲታይ ምንም እንኳን የፖሊሲና የስትራቴጂ ችግር ባይኖርበትም ከአፈጻጸም ጋር በተያያዘ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ችግሮች ተስተውሎበታል። ለዚህም ተቋሙ ካለበት የፋይናንስና ሌሎች ተያያዥ የቴክኒክ ችግሮች በተጓዳኝ በዋነኛነት አባል አገራት በኅብረቱ ቻርተር በመመራት ረገድ በርካታ ክፍተቶች መኖራቸው መረጃዎች ያሳያሉ።

በተለይም በጸጥታና ደኅንነት ምክር ቤት በኩል የሚወስናቸው ስምምነቶች ገቢራዊ አለመሆናቸው ትልቅ ክፍተት ሲሆን ምክር ቤቱም በቅርቡ ያደረገው ስብሰባ ይህንኑ አጋልጧል። ይህም አፍሪካ ኅብረት በአህጉሪቱ መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲ እንዲጎለብት በማድረግ ረገድ ያለው ቁርጠኝነት ልዩ ትኩረት የሚሻ መሆኑን አመላክቷል።

ለአብነትም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2020 የጥይት ድምፅ የማይሰማባት አህጉር ለመፍጠር ያቀደው ዕቅድ ምንም እንኳን ዕቅዱ ከጅምሩም ቢሆን ያለው ነባራዊ ሁኔታና የግጭቶች የመስፋፋት አዝማሚያ ከግምት በማስገባት ሊሳካ እንደማይችል በርካታ የመስኩ ተንታኞች ቢናገሩም ኅብረቱ በዚህ ረገድ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት አልቻለም። ለዚህም ደግሞ በቀዳሚነት ምንም እንኳን የአባል አገራት የፖለቲካ ቁርጠኝነት ማነስ ትልቁን ድርሻ ቢይዝም የሚወስዳቸው እርምጃዎች ሳይሸራረፉ ተግባራዊ ለማድረግ መቸገሩን ነው የሚያሳዩት።

በአፍሪካ በሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ ሥራዎች በቁርጠኝነት መሥራት ይገባል። በተለይም ደግሞ አፍሪካ ኅብረት በቅርቡ ዳግም የከለሰውን በአህጉሪቱ የጥይት ድምፅ ለማጥፋት የወጣውን ፍኖተ- ካርታና እንዲሁም የክትትልና የግምገማ ማዕቀፍ ፈጥኖ ወደ ሥራ ማስገባት ይኖርበታል። ይህንንም ተከትሎ በጸጥታና የደኅንነት ምክር ቤቱ ያቋቋመውን የባለሙያዎች ቡድን የያዘ ማዕቀብ ለመጣል የሚሰራው ንዑስ ኮሚቴም በአግባቡ መጠቀም አለበት።

አሁን ላይ በአህጉሪቱ ለጸጥታ መስፈን ሥጋት በሚሆኑና በሚያቆጠቁጡ ጉዳዮች ላይ እልባት ለመስጠት መረባረብ እንዳለበት ነው የሚጠቀሰው። በተመሳሳይ የሚወስዳቸው እርምጃዎችም በባህሪያቸው ተከታታይነትና ወጥነት ያላቸው እንዲሁም ችግሮች ከተፈጠሩ በኋላ ሳይሆን ከመፈጠራቸው በፊት አስቀድሞ መከላከልና ማክሸፍ ላይ ሊረባረብ እንደሚገባ ነው የሚያነሱት።

ከዚህ በተጓዳኝ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ለማፋጠን የሚያስችሉ የአገራትን የፖለቲካ እንቅስቃሴ መደገፍና በዘላቂነት ዴሞክራሲ ባህል እንዲሆን የሚያስችሉ ሥራዎችን መደገፍ እንዳለበትም ነው የሚነሳው። በተለይም ደግሞ ወጣቶችን ያሳተፉ የዴሞክራሲ ግንባታ ሥራዎች በስፋት መሠራት እንዳለበት ነው የሚጠቀሱት። ከዚህ ጎን ለጎንም የአፍሪካ የእርስ በርስ መገማገሚያ መድረክም (ፒር ሪቪው ሜካኒዝም) በተለይም መልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲጎለብት በማድረግ ረገድም አበርክቶው ከፍ እንዲል መሠራት ይጠይቃል።

የሰላም ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችለውን የሰላም ፈንድም ማሰባሰብ እንዳለበትም ነው የሚነሳው። ባሳለፍነው የፈረንጆች ዓመት አጋማሽ ላይ የሰላም ፈንዱ አጠቃላይ ገቢ 328 ሚሊየን ዶላር የደረሰ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 22 አባል አገራት ሙሉ በሙሉ እንዲሁም አምስት አገራት ደግሞ በከፊል የሚጠበቅባቸውን መዋጮ አዋጥተዋል። በሌላ በኩል 28 አባል አገራት ደግሞ መዋጮውን መክፈል አለመቻላቸውን ነው የአፍሪካ ኅብረት የሰላምና ደኅንነት ሪፖርት የሚያመለክተው። በመሆኑም አፍሪካ ኅብረት አባል አገራት የሚያዋጡትን ገንዘብ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ እንዲጨርሱ ቅስቀሳ ማድረግን በአፍሪካ ጥላ ሥር በተለያዩ አገራት የሚያንቀሳቅሰውን የሰላም ሥራ ውጤታማ ማድረግ ይገባዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት(ተ.መ.ድ) የጸጥታ ምክር ቤት ጉዳይ

ላለፉት 15 ዓመታት በአፍሪካ መሪዎች በስፋት የተቀነቀነው አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ሊኖራት ይገባል የሚለው ጉዳይም አፍሪካ ኅብረት በዘንድሮ ጉባዔው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። ምክር ቤቱ ከሚመለከታቸው ጉዳዮች ውስጥ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት አፍሪካን የተመለከቱ መሆናቸውና ይህም ሆኖ በምክር ቤቱ ውስጥ አፍሪካ አለመወከሏ የፍትሃዊነት ጥያቄ ሲያስነሳ ቆይቷል።

በርካታ የአፍሪካ መሪዎች እንዲሁም ኅብረቱን በሊቀ-መንበርነት የመሩት እስከ ወቅቱ ሊቀ-መንበር የሴኔጋሉ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ድረስ ጥሪያቸውን በተለያዩ መድረኮች አሰምተዋል። አሁን አሁን ላይም ጥያቄውን ምንም እንኳን የሩቅ ምስራቆቹ ጃፓንና ቻይና እንዲሁም ሕንድ አስቀድመው ቢቀበሉትም በተለይም አንዳንድ የምዕራብ አገራት ያሏቸውን የሃሳብ እቀባ በማንሳት ጉዳዩን እንዲጋሩት በማድረግ አፍሪካ ትልቅ ስኬት አግኝታለች።

ይህም ሆኖ አሁንም አፍሪካ ስንት መቀመጫ ይኑራት? እንዲሁም ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ይሰጣት ወይስ አይሰጣት? የሚለው ጉዳይ ላይ ክርክሮቹ እንደቀጠሉ ነው። በዘንድሮ ጉባዔው ኅብረቱ በእነዚህ ጉዳይ ላይ ተወያይቶ ወደ መጨረሻ ምዕራፍ ላይ የሚደረስበትን ውሳኔ ያስተላልፋል ተብሎ ይጠበቃል።

ይህንንም ማድረግ ከተቻለ በአፍሪካ ቀደምት መሪዎች ሲቀነቀን የቆየውን "አፍሪካዊ መፍትሔ ለአፍሪካ ችግሮች" የሚለውን ብሂል እውን ለማድረግና አህጉሪቷ ላይ ዘላቂ ሰላምና ደኅንነትን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ላይ አዎንታዊ አበርክቶ እንደሚኖረው ታምኖበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም