የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ አርሶ አደሮች የሀር ትል በማምረት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ስራ እየሰራ መሆኑን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ አርሶ አደሮች የሀር ትል በማምረት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ስራ እየሰራ መሆኑን ገለጸ
ሚዛን አማን (ኢዜአ) የካቲት 06 ቀን 2015 የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ አርሶ አደሮች የሀር ትል በማምረት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል የምርምር ስራ እየሰራ መሆኑን ገለጸ።
የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አብዮት አስረስ እንዳሉት ዩኒቨርስቲው ለአካባቢው አርሶ አደሮች ተስማሚ የሚሆኑ የምርምር ሥራዎችን የማስተዋወቅ ሥራ እየሰራ ነው።
የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የሀር ትል በማምረት የተለያዩ አልባሳትን ሰርቶ በማሳየት አርሶ አደሮች ወደ ሥራው እንዲገቡ እያደረገ እንደሆነም ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው ባደረገው ምርምር የሀር ትል ልማት ከአካባቢው አፈርና አየር ጸባይ ጋር የሚስማማና ውጤታማ መሆኑ እንደተረጋገጠ ገልጸው፤ አርሶ አደሩ በስፋት ቢሰራበት ተጠቃሚነቱን ስለሚያረጋግጥ ዩኒቨርሲቲው ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ በተካሄደው የሀር ትል የማምረት ሙከራ ሥራ የተለያዩ አልባሳትን በሽመና መዘጋጀቱንና ተደራጅተው ለሚመጡ ወጣቶች በዘርፉ የሥራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱን ብሎም አርሶ አደሩ በማሳው እንዲያመርት ተገቢውን ሥልጠና እንሰጣለን ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው የሀር ትል የሚያመርቱ፣ ወደ ጨርቅ የሚቀይሩና አልባሳት የሚሰሩ ሦስት ማኅበራትን ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በማደራጀት ሥራውን እንደሚያስፋፋም ተናግረዋል።
ከተለያዩ የጨርቃጨርቅ ማምረቻ ድርጅቶች ጋር የገበያ ትስስር የመፍጠር ሥራ እንደሚሰራ ገልጸው፤ ሥራው በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የተፈጥሮ ሀብትን በማልማት ለኢንዱስትሪ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በበቂ መጠን ለማምረት በምርምር የተደገፈ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።
በዘርፉ ምርምር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው መምህር ብዙነህ አድነው እንደገለጹት፤ የሀር ትል ምርት በዓመት ከአምስት ጊዜ በላይ ምርት የሚሰጥ በመሆኑ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የማድረግ ከፍተኛ አቅም አለው።
የሀር ትል ልማት ክር ከማስገኘት ባለፈ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቅሰው፤ ተረፈ ምርቱ ለዶሮና ዓሣ መኖ እንዲሁም የአፈር ለምነትን የሚጠብቅ ማዳበሪያ እንደሚገኝበት ገልጸዋል።
አርሶ አደሮች ከሌሎች የአዝዕርት ምርቶቻቸው ጋር በማሰባጠር አምርተው መጠቀም እንደሚችሉም በማስረዳት የምርምር ውጤቶች በሰርቶ ማሳያ ደረጃ ብቻ ታይተው እንዳይጠፉ ለማኅበረሰቡ ለማሰራጨት በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።