የወልዲያ ዶሮ ግብር ኤሌክትሪክ ሃይል ማከፋፈያ ጣቢያ መልሶ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት በቃ - ኢዜአ አማርኛ
የወልዲያ ዶሮ ግብር ኤሌክትሪክ ሃይል ማከፋፈያ ጣቢያ መልሶ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት በቃ
ወልዲያ የካቲት 6/2015(ኢዜአ) ጉዳት ደርሶበት የነበረው የወልዲያ ዶሮ ግብር ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ በመልሶ ግንባታ ለአገልግሎት መብቃቱን የኢትዮጰያ ኤሌክትሪክ ሃይል አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮንስትራክሽን ሥራ መምሪያ እና የግንባታ ሳይቱ ኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራ አስኪያጅ አቶ አብርሃም አባተ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ጣቢያው በጦርነቱ ወቅት በደረሰው ጉዳት የተወሰኑ የአማራና አፋር ከተሞች የኤሌክትሪክ ኃይል ሳያገኙ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
ነገር ግን በሰፈነው ሰላምና መንግስት ለመልሶ ግንባታው በሰጠው ልዩ ትኩረት መሰረት የሃይል ማከፋፈያ ጣቢያውን ቀድሞ ከነበረው በተሻለ ደረጃ መልሶ በመገንባት ለአገልግሎት ማብቃት መቻሉን ገልጸዋል።
በዚህም ጣቢያው ቀደም ሲል ከነበረው ባለ 50 ሜጋ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመር ወደ 63 ሜጋ ቮልት አምፒር ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር በላይ ኃይል ተቋርጦባቸው የቆዩ በአማራና አፋር የሚገኙ የሃራ፣ ድሬ ሮቃ፣ አረሪት፣ አለሌ ሱሉላ፣ ጭፍራ እና ሌሎች ከተሞች ከትላንት የካቲት 5 ቀን 2015 ዓ.ም ምሽት ጀምሮ በቂ የሃይል አቅርቦት ማግኘታቸውን አስረድተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የሃይል መቆራረጥ የነበረባቸው የወልዲያ ከተማን ጨምሮ የሳንቃና በቅሎ ማነቂያ ከተሞችን የሃይል አቅርቦት ችግር የሚፈታ መሆኑንም ተናግረዋል።
አሁን ላይ የማከፋፋያ ጣቢያው አንድ ባለ 230 ኪሎ ቮልት ገቢ መስመር ሲኖረው፤ አምስት ባለ 33 ኪሎ ቮልት እና አምስት ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች እንዳሉትም ገልፀዋል።
የጣቢያው መልሶ ግንባታ ሚያዝያ ወር 2014 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን በተቀናጀ አግባብ በተደረገ ያልተቋረጠ ርብርብ የካቲት 5 ቀን 2015 ዓ.ም በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ማብቃት እንደተቻለም ጠቅሰዋል።
ለጣቢያው መልሶ ግንባታ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከአሁን በኋላ በአካባቢው የኃይል አቅርቦት ችግር እንደማይኖር አቶ አብርሃም አስታውቀዋል።
የተፈጠረውን የሃይል አቅርቦት መቋረጥ በመረዳት እስካሁን በትዕግስት ሲጠባበቁ ለነበሩ ደንበኞችም ምስጋና አቅርበዋል።
የሃራ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ሙሉ ጎበና በሰጡት አስተያየት እንጀራ ጋግረው የሚተዳደሩ በመሆናቸው ችግሩ በኑሯቸው ላይ ጫና አሳድሮ መቆየቱን ጠቅሰው፤ መብራት በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።