በፕሪሚየር ሊጉ ወላይታ ዲቻ እና ሲዳማ ቡና ያደረጉት ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል - ኢዜአ አማርኛ
በፕሪሚየር ሊጉ ወላይታ ዲቻ እና ሲዳማ ቡና ያደረጉት ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል
አዲስ አበባ(ኢዜአ) የካቲት 6/2015 በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ11ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ወላይታ ዲቻ እና ሲዳማ ቡና አንድ አቻ ተለያይተዋል።
በድሬዳዋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ አማኑኤል እንዳለ በ11ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ግብ ሲዳማ ቡናን መሪ አድርጋ ነበር።
ይሁንና ዘላለም አባቴ ከሰባት ደቂቃ በኋላ ከመረብ ላይ ያሳረፋት ግብ የጦናዎችን ንቦች አቻ አድርጓል።
ውጤቱን ተከትሎ ወላይታ ዲቻ ነጥቡን ወደ 20 ከፍ በማድረግ በነበረበት አምስተኛ ደረጃ ላይ ረግቷል።
በአንጻሩ ሲዳማ ቡና በ13 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዞ አሁንም ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
በተያያዘም በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ያደረጉት ጨዋታ 1 ለ 1 በሆነ ውጤት መጠናቀቁ ይታወቃል።