ቀጥታ፡

በፕሪሚየር ሊጉ ወላይታ ዲቻ ከሲዳማ ቡና ይጫወታሉ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 5/2015 በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ11ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ወላይታ ዲቻ ከሲዳማ ቡና ዛሬ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በድሬዳዋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከቀኑ 11 ሰአት ላይ ይካሄዳል።

በአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም የሚመራው ወላይታ ዲቻ 12 ጨዋታ አድርጎ አምስት አሸንፎ ሶስት ጊዜ ተሸንፏል። አራት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።11 ግብ አስቆጥሮ 11 ጎሎች ተቆጥረውበታል። ያለ ምንም የግብ ክፍያ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በአንጻሩ በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ የሚሰለጥነው ሲዳማ ቡና 12 ጨዋታ አድርጎ ሶስት ሲያሸንፍ ስድስት ጊዜ ተሸንፏል።

ሶስት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል። 15 አግብቶ 25 ተቆጥሮበታል። በ10 የግብ እዳ 14ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ወላይታ ዲቻ ባለፉት አምስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ሶስት አሸንፎ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።

ሲዳማ ቡና ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ያሸነፈው አንድ ጊዜ ብቻ ነው።ሁለት ጊዜ ተሸንፎ ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።

ፌደራል ዳኛ ቢኒያም ወርቅአገኘሁ የሁለቱን ክለቦች ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

በተያያዘም ትናንት በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ቡና አንድ አቻ ተለያይተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም