በዱባይ ማራቶን ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታዎች አሸነፉ - ኢዜአ አማርኛ
በዱባይ ማራቶን ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታዎች አሸነፉ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 5/2015 በዱባይ ማራቶን ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታዎች አሸናፊ ሆነዋል።
ዛሬ ማለዳ በተደረገው ውድድር በወንዶች ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ከ1 እስከ 10 እንዲሁም በሴቶች ከ1 እስከ 8 በመውጣት ፍጹም የበላይነትን ይዘዋል።

በወንዶች አትሌት አብዲሳ ቶላ 2 ሰዓት ከ5 ደቂቃ ከ42 ሴኮንድ ውድድሩን በመጨረስ አሸንፏል።
አትሌት አብዲሳ በአሜሪካ ኦሬጎን በሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በወንዶች ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘው አትሌት ታምራት ቶላ ታናሽ ወንድም ነው።
አትሌት ደሬሳ ገለታ እና አትሌት ሃይማኖት አለው ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ይዘዋል።
በሴቶች አትሌት ደራ ዲዳ 2 ሰዓት ከ21 ደቂቃ ከ11 ሴኮንድ በመግባት የውድድሩ አሸናፊ ሆናለች።

አትሌት ደራ የአትሌት ታምራት ቶላ ባለቤት ነች።አትሌት ሩቲ አጋ እና አትሌት ስራነሽ ይርጋ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን አጠናቀዋል።
በሁለቱም ጾታዎች ያሸነፉት አትሌቶች በተመሳሳይ የ80 ሺህ ዶላር ሽልማት ያገኛሉ።
በተያያዘ ዜና ዛሬ ማለዳ በተካሄደው የሆንግ ኮንግ ማራቶን በሴቶች አትሌት ፋንቱ ኢቲቻ 2 ሰዓት ከ27 ደቂቃ ከ51 ሴኮንድ በመግባት አሸንፋለች።
ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊ አትሌት ስንቄ ደሴ ሁለተኛ ወጥታለች።በወንዶች ኬንያዊው አትሌት ፊልሞን ኪፕቶ ኪፕቹምባ አሸንፏል። ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች ልመንህ ጌታቸው እና ሰንበታ ገዛ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።