ቀጥታ፡

ማርቺንግ ባንድ በትምህርት ቤቶች ቢጠናከሩ ለኢትዮጵያ የሙዚቃ ዕድገት ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል - የሙዚቃ ባለሙያ ዳዊት ይፍሩ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 04/2015 ማርቺንግ ባንድ በትምህርት ቤቶች ቢጠናከሩ ለኢትዮጵያ የሙዚቃ ዕድገት ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል ሲል የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበራት ዘርፍ ፕሬዝዳንት ዳዊት ይፍሩ ተናገረ።

የሙዚቃ ባለሙያዎቹ ይህን የገለጹት የዳግማዊ ምኒልክ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የማርቺንግ ባንድና የዘመናዊ ባንድ ኦርኬስትራ 35 ተማሪዎችን በዛሬው ዕለት ባስመረቀበት መርሐ-ግብር ላይ ነው።

የትምህርት ቤቱ የማርቺንግ ባንድ መምህር ሌተናል ኮሎኔል ሲሳይ ፍቃዱ እንደገለጹት፤ ማርቺንግ ባንድ በአገሪቱ የተወሰኑ ትምህርት ቤቶች የነበረና መሃል ላይ የተቋረጠ እንደሆነ ገልጸዋል።

በመሆኑም ይህ የባንድ እንቅስቃሴ ዳግም እንዲያንሰራራ በመነሳሳት የዳግማዊ ምኒልክ ተማሪዎችን በመሰብሰብ ከ40 ዓመት በኋላ ትምህርት ቤቱ የማርቺንግ ባንድ ተማሪዎችን ማስመረቅ መቻሉን ተናግረዋል።

በትምህርት ቤቶች ማርቺንግ ባንዶችንና ዘመናዊ ኦርኬስትራን ማጠናከር ለኢትዮጵያ የሙዚቃ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለውም ባለሙያው ይናገራሉ።

በኃይለሥላሴ እና በደርግ ዘመነ-መንግሥትም በትምህርት ቤቶች የባንድ እንቅስቃሴ መኖር ትልቅ ሙዚቀኞች እንዲወጡና ለኢትዮጵያ ሙዚቃ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ እንዳደረገ ተናግረዋል።

ለዚህም እንደ ዳግማዊ ምኒልክ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና በድሬደዋ የነበረው የተማሪዎች ማርቺንግ ባንድ ለአብነት ማንሳት እንደሚቻል ገልፀዋል።

አሁንም ከሁለት አሥርት ዓመታት በኋላ የተመረቁት የዳግማዊ ምኒልክ የማርቺንግ ባንድ ተማሪዎች የተዳከመውን የትምህርት ቤቶች የማርቺንግ ባንድ መልሶ እንዲያንሰራራ መነሻ እንደሚሆን ተናግረዋል።

በተለይ በግለሰቦች መልካም ፍቃድ ብቻ መደገፉ ቀርቶ እንደ አንድ የትምህርት ሥርዓት በትምህርት ቤቶች ቢካተትና ትምህርቱ ቢሰጥ የተሻለ መሆኑን ጠቁመዋል።

የመከላከያ ሙዚቃ ኮሌጅ ዲን ሙዚቀኛ ዮሴፍ ይርሳው በበኩላቸው፤ የማርቺንግ ባንድና ዘመናዊ ባንዶችን በትምህርት ቤቶች ማጠናከር ሙዚቃን ከልጅነት ዘመን ተዋውቆ የተሻለ ባለሙያ ለመሆን እንደሚያበቃ ተናግረዋል።

ለማርች ባንዶችና ለዘመናዊ ኦርኬስትራም የባለሙያና የሙዚቃ መሣሪያ እጥረትም ስለሚያጋጥም የግለሰቦች ጥረት ብቻ ሳይሆን የመንግሥት፣ የተለያዩ የተቋማትና፣ የባለሃብቶች ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል።

በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሙዚቃ ክፍለ ጊዜ እየተባለ የሚሰጠውም ትምህርት ሙዚቃን በሚገባ ባጠኑ መምህራን ቢሰጥ መዝሙር ከማዘመር ባለፈ ለማርቺንግ ባንድ አስተዋፅኦ እንዳለው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበራት ዘርፍ ፕሬዝዳንት ዳዊት ይፍሩ ለማርቺንግ ባንድ የፖሊስ ሠራዊት፣ ክቡር ዘበኛ፣ አገር ፍቅርና ብሔራዊ ቴአትር ብቻ ሳይሆኑ ትምህርት ቤቶች አስተዋፅኦ ነበራቸው ብለዋል።

ለዚህም እንደ ዳግማዊ ምኒልክ፣ ኮከበ ፅባህ፣ በአዳማ የሚገኘው ገላውዲዮስ ትምህርት ቤትና ወሎ የሚገኘው ወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤቶች ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልፀዋል።

እንደ ሳንፎርድ ያሉ የግል ትምህርት ቤቶችም ውስጥ የማርች ባንድ እንዳለ በምሳሌነት አንስተዋል።

ስለሆነም ማርቺንግ ባንዶች በትምህርት ቤቶች ቢጠናከሩ ለኢትዮጵያ የሙዚቃ ዕድገት ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል ነው ያሉት።

በተለይ የማርቺንግ ባንዶች በትምህርት ቤቶች መጠናከር ወላጆች ለልጆቻቸው ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ሙዚቃ እንዲማሩና ተሰጧቸውን እንዲያወጡ ነፃነት እንዲሰጧቸው ያግዛል ብለዋል።

አብዛኛው ወላጅ ልጆች የሙዚቃ ትምህርት ቢማሩ ከትምህርታቸው እንደሚዘናጉና የትምህርት ውጤት ሳይመጣላቸው ሲቀር የሚገቡበት ዘርፍ አድርገው የሚመለከቱትን አመለካከት ያስተካክላል ነው ያሉት።

የሙዚቃ ትምህርት እንደ ስፖርትና ሒሳብ ትምህርት ተደጋጋሚ ልምምድ ስለሚጠይቅ ተመራቂ ተማሪዎች ከምረቃ በኃላ የተማሩትን በተግባር እንዲያውሉ በሥራ እንቅስቃሴ ውስጥ መሆን እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም