የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አገራዊ የወጣቶች ምክር ቤት ለማቋቋም በዝግጅት ላይ መሆኑን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አገራዊ የወጣቶች ምክር ቤት ለማቋቋም በዝግጅት ላይ መሆኑን ገለጸ
አዳማ (ኢዜአ) የካቲት 04/2015 የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚያረጋገጥ አገራዊ የወጣቶች ምክር ቤት ለማቋቋም በዝግጅት ላይ መሆኑን ገለጸ።
ምክር ቤቱን 'የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት' በሚል ስያሜ ለማቋቋም የተዘጋጀውን ሰነድ ለማዳበር ያለመና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ህብረት አባላትና አመራሮች የተሳተፉበት መድረክ በአዳማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙና አህመድ እንደገለፁት፤ የወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት የተረጋገጠበት የአገር ልማት፣ ዕድገትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ ወጣቱ ሃይል የራሱን ችግር በራሱ የሚፈታበት ጠንካራ አደረጃጀት መገንባት ማስፈለጉን ተናግረዋል።
ወጣቶች ያላቸውን እምቅ አቅም፣ ክህሎትና ዕውቀት ተጠቅመው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡ የሚያስችል አደረጃጀት መፈጠር አለበት ብለዋል።
አሁን ያለው የወጣቶች አደረጃጀት የወጣቱ ድምፅ ከመሆን፣ መብትና ጥቅሙን ከማስጠበቅ አንፃር ክፍተት እንዳለበት ጠቅሰው፤ የወጣቶች ፍላጎትና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች በትክክል የተቃኘበትና ተሞክሮዎች የተካተቱበት የወጣቶች ምክር ቤት ማደራጀት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ ሲቋቋም ወጣቶች በራሳቸው ጉዳይ ላይ እንዲወስኑ፣ ችግሮቻቸውን በራሳቸው እሳቤና መንገድ እንዲፈቱ የሚያስችል ዕድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
አሁን ያለው የወጣቶች አደረጃጀት ወጣቶች የዴሞክራሲ ልምምድ እንዲኖራቸው፣ በበጎ ፍቃድ አገልግሎትና ሰብዓዊ ድጋፍ ተሳትፎ የተሻለ ስራዎች የሰራ ቢሆንም ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን ያገናዘበ የአደረጃጀት ማሻሻያ እንደሚፈልግ ተናግረዋል።
በዚህም አሁናዊ የወጣቶች አደረጃጀት ያለበትን ቁመና ለማወቅ ሚኒስቴሩ የዳሰሳ ጥናት ማካሄዱን የገለፁት ወይዘሮ ሙና፤ በጥናቱ ውጤት መሰረት የዓለም ሀገራት ልምድና ተሞክሮዎች የተካተቱበት ጠንካራ የወጣቶች አደረጃጀት መፍጠር ማስፈለጉ ታምኖበት ሰነዱ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
መንግስት ለሚቋቋመው ምክር ቤት ተገቢውን ድጋፍና ክትትል ያደርጋል ነው ያሉት ።
ምክር ቤቱ በመጪው መጋቢት ወር 2015 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ይመሰረታል ተብሎ ይጠበቃል።
የምክር ቤቱ መቋቋም የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የወጣቶች አደረጃጀት ለመገንባት ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት የአስተዳደር ጉዳዮች ዴስክ ሃላፊ አቶ አብዱ ናስር ገልጸዋል።
የወጣቶች ጠንካራ አደረጃጀት መኖር ምክንያታዊ ወጣትነት መርህን በመከተል የሀገር ልማትና ዕድገት ለማረጋገጥ ምቹ መደላድል የሚፈጥር ነው ብለዋል ።