ቀጥታ፡

ለፖሊስ ሠራዊት አባላት አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ 54 የሕክምና ተቋማትን ወደ 90 ለማድረስ እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው-የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 4/2015 ለፖሊስ ሠራዊት አባላት አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ 54 የሕክምና ተቋማትን ወደ 90 ለማድረስ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።

ተቋሙ 60ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓሉን ከፍተኛ የሠራዊቱ አባላት በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ተቋሙ እስካሁን የፖሊስ አባላትና ቤተሰቦቻቸውን እንዲሁም በፖሊስነት ላገለገሉ አባላት ህክምና እየሰጠ ይገኛል።

ተገቢውን የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ አገራዊ ግዳጃቸውን በብቃት እንዲወጡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።

ከጊዜ ወደ ጊዜም ተደራሽነቱ እያደገ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራቱም እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመዋል።

በተለያዩ ፖሊሳዊ ግዳጆች ተሰማርተው ጉዳት የደረሰባቸው የሰራዊቱ አባላት አገግመውና ሙያዊ ሥልጠናዎችን ወስደው አምራች እንዲሆኑ የሚያስችል ማዕከል እየተገነባ መሆኑን ገልጸዋል።

ማዕከሉ በቅርቡ ተጠናቆ ሥራ እንደሚጀምር የገለጹት ኮሚሽነሩ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች 4 የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ለማስገንባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን ላይ ያሉትን 54 የጤና ተቋማት ወደ 90 ለማድረስ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የጤና ሚንስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው ተቋሙ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራቱን ለማሳደግ ሌት ተቀን የሚሰራ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።

እንዲሁም የሚገነቡ ተቋማት ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ለሚደረገው ጥረት ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

መስዋዕትነት እየከፈለ ለሚገኘው ሠራዊት ደረጃውን የጠበቀ ሕክምና ማግኘት ይገባዋል ያሉት ሚንስትሯ ለዚህም አስፈላጊውን ድጋፍ ሚንስቴሩ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

ሆስፒታሉን በህክምና ቁሳቁሶች በማደራጀት ዘመኑ የደረሰበትን የህክምና አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የፌዴራል ፖሊስ የጤና አገልግሎት ዋና መምሪያ ሃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ዶክተር ደረጀ ተካልኝ ናቸው።

ተቋሙ የአገልግሎት ተደራሽነቱን ለማስፋት በተለያዩ አካባቢዎች መሬት ተረክቦ እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የሆስፒታሉን የአገልግሎት ደህንነት ከማስጠበቅ አንጻር የበሽታ መከላከልና የጤና ማበልጸግ ክፍል ተከፍቶ ወደ ሥራ መግባቱን ጠቁመዋል።

በሀረር የሚገኘውን ሆስፒታል በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የማስፋፊያ ፕሮጀክት ተቀርጾ ወደ ሥራ መግባቱን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ሪፈራል ሆስፒታል ከተመሰረተበት 1954 ዓ.ም ጀምሮ ለሰራዊቱ አባላት የህክምና አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ አንጋፋ ተቋም ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም