የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ባለፉት ስድስት ወራት 3 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ገቢ አገኘ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ባለፉት ስድስት ወራት 3 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ገቢ አገኘ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 04/2015 የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ባለፉት ስድስት ወራት ከተለያዩ ፕሮጀክቶች 3 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱን ገለጸ።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው ኮርፖሬሽኑ ባለፉት ስድስት ወራት ያከናወናቸውን ተግባራት በተመለከተ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ኮርፖሬሽኑ በግማሽ ዓመቱ በኮንስትራክሽንና በሌሎች ዘርፎች 3 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ገቢ ለማግኘት አቅዶ 3 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ማግኘት ችሏል ብለዋል።
ኮርፖሬሽኑ ገቢውን ያገኘው ከህንፃ ግንባታ፣ ከመንገድና ድልድይ ግንባታ እንዲሁም ከውሃ ኃብት ልማት ግንባታ ፕሮጀክቶች ነው።
ከተገኘው ገቢ ውስጥ 306 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚሆነው ያልተጣራ ትርፍ መሆኑን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ኮርፖሬሽኑ አሁን ላይ 30 የህንፃ፣ 23 የመንገድና የድልድይ ግንባታና ስምንት የውሃ ኃብት ልማት ግንባታ ፕሮጀክቶችን በአጠቃላይ 61 ፕሮጀክቶችን በ45 ነጥብ 2 ቢለየን ብር እያከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በአጠቃላይ የኮርፖሬሽኑ የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም በህንፃ፣ በመንገድና ድልድይ እንዲሁም በውሃ ኃብት ልማት ፕሮጀክቶች 90 ነጥብ 3 በመቶ መድረሱን ጠቁመዋል።
ከህንፃ ግንባታ አኳያም በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ሥፍራዎች በርካታ ግንባታዎችን በማጠናቀቅ አገልግሎት እንዲሰጡ የተደረገበት ሁኔታ መኖሩን አስረድተዋል።
ኮርፖሬሽኑ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በርካታ ተገጣጣሚ ቤቶችን ለመሥራት ውል ወስዶ ሥራውን እያከናወነ እንደሚገኝ ተመልክቷል።